
ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመውጫ ፈተና መመዝገቢያ ጊዜ እስከ ጥር 20 2016ዓ.ም መራዘሙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በ2016 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ለመፈተን የምዝገባ ጊዜው ጥር 08/2016 ዓ.ም ጀምሮ ጥር 15/2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ማሳወቁን አስታውሷል።
በተፈታኞች ጥያቄ መሰረት የምዝገባ ጊዜው እስከ ጥር 20 2016 ዓ.ም ድረስ ተራዝሟል ብሏል። ሌሎች ሁኔታዎች ግን ቀደም ሲል በተገለጸው አግባብ የሚከናወኑ መሆኑን እናሳውቃለን ነው ያለው።
ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም በቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ለእጩ ተመራቂ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የመውጫ ፈተናን ለመፈተን በመጠባበቅ ላይ ያላችሁ ተፈታኞች በሙሉ ፈተናው ከጥር 27- የካቲት 1/2016 ዓ.ም ይሰጣል ተብሏል።
በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተናውን ተፈትናችሁ ያላለፋችሁ እና ከጥር 27 – የካቲት 1/ 2016 ዓ.ም ድረስ የመውጫ ፈተናውን በድጋሚ (Re-exam) ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ያላችሁ ተፈታኞች በሙሉ ምዝገባ የምታካሂዱትና የመፈተኛ ተቋም (የመንግስት ዩኒቨርሲቲ) የምትመርጡት ከታች በተገለጸው ማስፈንጠሪያ (Link) ነው።
(https://exam.ethernet.edu.et)
ስለሆነ፣ ከጥር 08 እስከ ጥር 20 2016 ዓ.ም ድረስ የምዝገባ ክፍያ 500.00 ብር በቴሌ ብር ብቻ በመክፈል መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን ነው ያለው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የመዉጫ ፈተና የምትፈተኑ እጩ ተመራቂዎች ምዝገባ የምታካሂዱት እና የአገልግሎት ክፍያ የምትፈፅሙት በተቋማችሁ በኩል ነውም ብሏል ትምህርት ሚኒስቴር።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
