
ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በጥናት በተለዩ 12 ዞኖች እና ስድስት ከተሞች የገበያ ማረጋጋት ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራቱን በባለሥልጣኑ የእቅድ፣ በጀት ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር መሳፍንት አሞኜ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የኑሮ ውድነት በተባባሰባቸው ዞኖች እና ከተሞች 84 የሸማቾች ኀብረት ሥራ ማኀበራት፣114 ሁለገብ የገበሬ ዩኒዬኖች፣ ስምንት የወተት ግብይት ማኀበራት እንዲሁም አራት በዶሮ እና እንቁላል አቅርቦት የተሰማሩ ማኀበራት ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ገበያ በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ግብይቶችን ፈጽመዋል ብለዋል።
ማኀበራቱ ከገበሬዎች ጋር በቀጥታ የምርት ትስስር በመፍጠርም ገበያን የማረጋጋት ሥራ አከናውነዋል ነው ያሉት። በተመረጡ አካባቢዎችም 417 ሺህ ኩንታል በቆሎ፣ 18 ሺህ ኩንታል ስንዴ እንዲሁም 14 ሺህ ኩንታል ጤፍ የምርት ትስስር በመፍጠር ለገበያ መረጋጋቱ መዋሉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው በክልሉ ውስጥ የሚገኙት ሁሉም የኀብረት ሥራ መኀበራት እና ዩኒዬኖች እንደ አቅማቸው ወደ ግብይት ሥራ በመግባት የኑሮ ውድነቱን ማርገብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት ።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው በክልሉ በርካታ የምግብ ዘይት እና የዱቄት ፋብሪካዎች እያሉ ማኀበረሰቡ በምግብ ዘይት እና በዳቦ እጦት የሚሰቃየው ምርቱ በማኀበራቱ በኩል በብዛት እና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ ባለመቻሉ ነውም ብለዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!