“ይድረስ ለመንግሥት” ቅሬታ ማቅረቢያ ነጻ የስልክ ጥሪ አገልግሎት በቅርቡ ሥራ ሊጀምር መኾኑ ተገለጸ፡፡

25

ባሕር ዳር: ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል መንግሥት የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ቅሬታ ማስተናገድ እና ውሳኔ መስጠት ዳይሬክተር ያረጋል አስፋዉ እንደገለፁት “ይድረስ ለመንግሥት” የቅሬታ ማስተናገጃ ሥርዓት በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ያለምንም ውጣ ውረድ እና ለተጨማሪ እንግልት ሳይዳረጉ ባሉበት ኾነው ቅሬታቸውን፣ አስተያየት፣ ጥቆማ እና ጥያቄያቸውን ማቅረብ የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።

ተገልጋዮች ያቀረቡት ቅሬታ ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበት ነጻ የስልክ መስመር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ መኾኑን ገልጸዋል።
ይድረስ ለመንግሥት ነጻ የስልክ ጥሪ አገልግሎት ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ አዲስ እና የመጀመሪያ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ በተመረጡ ዞን እና ወረዳ አሥተዳደሮች ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን አንስተዋል። አገልግሎቱ 249 የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ያረጋል አስፋው ገልጸዋል።

ይድረስ ለመንግሥት ነጻ የስልክ ጥሪ አገልግሎት የዜጎችን ውጣ ውረድ፣ እንግልት እና ድካም ለመቀነስ እንዲሁም ወጭ እና ጊዜያቸውን እንደሚቆጥብ ጠቁመዋል። ተቋማት የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ተጠያቂነት እንዲኖር እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አገልግሎት አሠጣጥን ለማሻሻል ቴክኖሎጂን መጠቀም አንዱ እና ዋነኛ መፍትሔ ነው ሲሉ አቶ ያረጋል ተናግረዋል። ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ተጠያቂነትን በማስፈን መረጃን በመሰብሰብ እና በማደራጀት በኩል የቴክኖሎጂው ሚና ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ይድረስ ለመንግሥት ቴክኖሎጅ አዲስ በመሆኑ ወደ ሥራ ለማስገባት በቀጣይም ሠፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደሚጠይቅ መናገራቸውን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት አሳውቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ታሪክና ሃይማኖት የሚነገርባት፣ ጥበብ የመላባት”
Next articleበአማራ ክልል የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወኑን የክልሉ የኀብረት ሥራ ማኀበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለጸ።