
ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለቀናት ታቦታት ከመንበራቸው እየወረዱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይጓዙባታል፣ ግርማ እና ሞገስን ያጎናፅፏታል። በዚያች ከተማ የሚገኙ ክርስቲያኖች በየቀኑ ለታቦታት ክብር ይሰጣሉ፣ ታቦታት የሚመላለሱባቸውን ጎዳናዎች ያስውባሉ፣ ለመረማመጃ ያማረውን ምንጣፍ ያነጥፋሉ፣ እልል እያሉ ይከበክባሉ፣ በአንደበታቸው ምሥጋናን ይመላሉ።
በቤተ መንግሥት የሰመረ፣ በታሪክ የከበረ፣ ከዳር ዳር ያሉ ወገኖችን ያስተሳሰረ፣ በአንዲት ኢትዮጵያ ያስጠለለ፣ ለአንዲት ሠንደቅ ያስማለ ዓለማዊ ሕግ ፀንቶባታል። በጭንቅ ዘመን የተገኘ፣ ዘመኑን የቀደመ፣ ከትናንት ወዲያ ኾኖ ከነገ ወዲያን ያለመ፣ በአጭር ዘመን ረጅም ዘመናትን የተለመ ታላቁ መሪ ቴዎድሮስ የክብሩ መቀመጫ አድርጓታል። ስለ ሀገሩ ፍቅር ፣ ስለ ሕዝቡም ክብር ከታማኝ የጦር አበጋዞቹ፣ ግርማ ከሚኾኑ መኳንንቶቹ እና መሳፍንቶቹ ጋር መክሮባታል። ከዘመን ረዘም ብሎ የሚታይ፣ ከተራራም የዘለለ ታሪክ ሠርቶባታል።
እርሱን ብለው ባሕር ሰንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው፣ ሀሩር እየበረታባቸው፣ ውርጭ እየጸናባቸው በፈረስ እና በእግራቸው የሚመጡትን የባሕር ማዶ እንግዶችን እየተቀበለ አስተናግዶባታል። የሀገሩን ክብር፣ የእርሱንም ራዕይና ሕልም ነገሮበታል። ለዘመኑ ፈጽሞ አዲስ የኾነ የጥበብ ሥራ አስጀምሮባታል ታሪካዊቷ ከተማ ደብረ ታቦር።
በዚህች ታሪካዊት ከተማ የበዙ ሊቃውንት ወጥተውባታል፣ የረቀቀውን ምስጢር ፈትተውባታል፣ የከበደውን አቅለውባታል፣ የተሰወረውን ገልጠውባታል። ሊቃውንቱ እንደ ዥረት እየፈሰሱ፣ ምድርን በጥበብ እያረሰረሱ ዛሬም መልተውባታል።
በዚህች ታሪክ በጠገበች፣ በብዙው በታደለች ከተማ ወረኃ ጥር በደረሰ ጊዜ ድንቅ ነገር ይደረጋል። በወረኃ ጥር አብዛኛዎቹ ቀናት ጥምቀት ናቸው። ሊቃውንቱ እና ምዕመናኑ ታቦታትን በማንገሥ እና በማወደስ ለቀናት ይዘልቃሉና። በዚህች ከተማ ለቀናት ታቦታት ይነግሳሉ።
ወረኃ ጥር ሲቀርብ ደብረ ታቦር ጎዳናዎቿን ታሰማምራለች፣ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ታስውባቸዋለች፣ ለታቦታት ማለፊያ የሚኾኑትን ታስጌጣቸዋለች። በዓለ ጥምቀት በደረሰ ጊዜ ታቦታቱ ከየአድባራቱ እየመጡ በአጅባር ሜዳ ያርፋሉ። ሕዝብ ሁሉ ይሰባሰባል። በዚያውም የከበረው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈፀማል። ሥርዓቱ ደርሶ በተፈፀመ ጊዜም ታቦታቱ በታላቅ አጀብ ወደየመንበራቸው ይመለሳሉ። በደብረታቦር ይህ ሥርዓት በአጅባር እና በሌሎች የታቦታት ማደሪያዎች እየተፈፀመ ለቀናት ይዘልቃል።
በደብረታቦር ከጥር 10 እስከ ጥር 29 ቀን ድረስ ከሌሎች አካባቢዎች ለየት ያለ ሥርዓት ይፈፀማል። ወደከተማዋ የሚመጡ ምዕመናን እና ሌሎች እንግዶች ሁሉ ጥምቀትን ያከብራሉ።
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ ደቡብ ጎንደር በቀደመ አጠራሩ በጌምድር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጉልላት ነው ይላሉ። ምክንያቱም የሊቃውንት መፍለቂያ ምንጭ ነው። ጥበብን የሚዘሩ ሊቃውንት ሲፈልቁበት ኖረዋል። ዛሬም እየፈለቁ ደቀመዛሙርትን እያጠጡ ያበቅላሉ።
ጳጳሳት ይወጡበታል። የአብነት ምስክር ጉባዔ ቤት መገኛ ነው፣ ቅድስት ቤተልሔም የድጓ ምስክር ጉባኤ ቤት፣ ደብረ ፅጌ ቆመ ቅዱስ ፋሲለደስ የቆሜ ድጓ ምስክር ጉባኤ ቤት፣ ደብረታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤት፣ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ የብሉያት፣ የሐዲሳት ምስክር ጉባኤ ቤት ያሉበት፣ እነ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቂርቆስ፣ እንደ ደብረ ልዑላን መድሐኔዓለም ቤተክርስቲያን እና ሌሎች የከበሩ አብያተክርስቲያናት እና ገዳማት የሚገኙበት ነው ይላሉ ሊቁ።
የታሪክ፣ የጥበብ እና የሊቃውንት ምንጭ ነውም ይላሉ። ሊቁ ሲናገሩ በዋና ከተማዋ በደብረ ታቦር የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትን መሠረት በማድረግ የጥምቀት በዓል ደምቆ ይከበራል፣ በማግሥቱ የቃና ዘገሊላ ወይም የሚካኤል ጥምቀት በአጅባር እና በደብረ ሳሂል ፀጉር ሚካኤል፣ በ13 አቡነ ዘርዓብሩክ ፣ በአሥራ ሦስት ወጥቶ በ14 አቡነ አረጋዊ፣ በ14 የቅዱስ ቂርቆስ ታቦት ከደብረ ልዑላን መድሐኔዓለም ወጥቶ እጃባር ያድራል፣ በዓሉም በ15 ደምቆ ይከበራል። በ17 የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርዶ ያድራል፣ በ18 ሰባሩ ጊዮርጊስ ደምቆ ይውላል። ይህም በዓል የሚከበረው በሦስት ሥፍራ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት እንደገባ የቅዱስ ገበርኤል ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ይወርዳል። በ19 በድምቀት ሲከበር ይውልና ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል።
በማግሥቱ በ20 ደግሞ የማርያም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ይወርዳል። በ21 የአስተርዮ ማርያም ደምቆ ይከበራል። የማርያም ታቦት እንደገባ፣ የቅዱስ ዑራኤል ታቦት ወደ ጥምቀት ባሕር ይወርዳል። በ22 በዓሉ ይከበራል። በ24 ደግሞ በከተማዋ እጅግ ደምቆ የሚከበረው እና በርካታ እንግዶችን የሚስበው የሰማዕቱ የቅዱስ ቂርቆስ ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርዶ በ25 ከፍ ብሎ፣ አምሮና እና ተውቦ ይከበራል። በከተማዋ የመጨረሻዋ ጥምቀት እየተባለ የሚጠራው ክብረ በዓል የቅድስት አርሴማ ታቦት በ28 ይወርዳል፣ በ29 ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል። ከጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ በዚያች ከተማ ጎዳናዎቿ በሰው እንደተመሉ፣ እንዳጌጡ ይሰነብታሉ። ይህም ለከተማዋ ልዩ ውበት እና ግርማ ነው።
ሊቁ ሲናገሩ ሃይማኖትን ከእነ ሥርዓቱ ከአበው ተቀብለናል፣ እርሱ በወደደ እና በፈቀደ ልክ እያከበርን ነው፣ እኛ ስናልፍም ለልጆቻችን እናስተላልፋለን፣ የከበረው ሥርዓትም ይቀጥላል ነው ያሉት። አጅባር ሜዳ ብቻ አይደለም ቤተመቅደስ እና የቤተክርስቲያን እርስት ነው ይሉታል። በሌሎች አካባቢዎች ከጥምቀት በኋላ ባሉት በበዓላት ቀን ታቦታት በዚያው ታውደው ይገባሉ፣ በደብረ ታቦር ግን በዋዜማውም ታቦታት ወርደው ሕዝብን እየባረኩ በአደባባይ ይከበራሉ ነው ያሉት።
በደብረ ታቦር ለቀናት የሚዘልቅ የጥምቀት በዓል ይከበራል። ሕዝብ ሁሉ ሳይቋረጥ ይባረካል። ታቦታትም ከመንበራቸው እየወጡ ሕዝብን ይባርካሉ፣ ሕዝብን ከፈተና እና ከመከራ ያሳልፋሉ ነው ያሉት። ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ለከተማዋ ውበት፣ ጌጥ እና ሃብት ነውም ይላሉ። ስለ ምን ቢሉ የበዙ እንግዶችን ይጠራሉና። በዓሉ ሁሉ በክብር እና በቅድስና እየተከበረ ይኖር ዘንድ ሥርዓቱ መጠበቅ ግድ ይለዋል ነው ያሉት ። ሊቁ ሁሉም ወደ ታሪካዊቷ ከተማ ደብረታቦር ይምጣ። በበዓላት ይቀደስ፣ አምላኩንም ያወድስ፣ የከበረ በዓላትን ያክብር ብለዋል።
በወርሐ ጥር ወደ ደብረታቦር የመጣ የተቀደሰ የሃይማኖት ሥርዓት ያያል፣ በዓላትን ያከብራልና። በዚያች ከተማ ጥር ወር ሁሉ ጥምቀት ነው እየተባለ ይጠራልና። አብዛኛው በዓል የሚከበረው ደግሞ በአጅባር ነው። ታሪክና ሃይማኖት የሚነገርበት፣ ታላላቅ ጉባኤያት የተደረጉበት ታላቅ ሥፍራ ነው። ሂዱ ለቀናት የማይቋረጥ በዓላትን ታደሙ። ሥርዓት እና ታሪክን እዩ፣ አይታችሁም ተደነቁ፣ ተገረሙም። ደብረ ታቦር የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የእሴት ማኅደር።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!