
ባሕር ዳር: ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አብደላ ነጋሽ እንዳሉት በግማሽ ዓመት ለውጭ ገበያ ከተላኩት የሆርቲካልቸር ሰብሎች 298 ሚሊዮን 794 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።
ለውጭ ገበያ ከተላኩት የሆርቲካልቸር ምርቶች መካከል 29 ሺህ 288 ቶን በላዩ የእንሰት እና ሥራሥር ምርት መሆኑን አመላክተዋል። በተጨማሪ 46 ሺህ 984 ቶን በላይ የአበባ፣ 21 ሺህ 276 ቶን በላይ የፍራፍሬ እና 74 ሺህ 336 ቶን በላይ የአትክልት እና እጣን ምርቶችን መላክ መቻሉን ገልጸዋል።
ወደ ውጭ ገበያ የተላኩት ምርቶች ከ2015 በጀት ዓመት ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከታቀደው በላይ መሆኑን አንስተዋል። የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አንጻር ግን ዝቅተኛ ገቢ የተገኘ መገኘቱን አመላክተዋል። በተለይም ወደ ውጭ የተላኩት የእንሰት እና ሥራሥር ምርቶች እንዲሁም የአበባ ምርቶች መቀነሳቸውን ጠቁመዋል። ገቢያቸውም በዚያው ልክ መቀነሱን አስታውቀዋል።
የገቢውን መቀነስ ምክንያት ለማጥናት ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በጋራ ጥናቶችን በማካሄድ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። አቶ አብደላ እንዳመላከቱት ምርቶቹ የሚላኩባቸው በርካታ የገበያ መዳረሻዎች አሉ። የአበባ ምርት ቀዳሚዋ የገበያ መዳረሻ ስዊዘርላንድ ስትሆን በሌሎችም ለአውሮፓ ሀገራት ገበያ ይቀርባል።
የእንሰት እና የሥራሥር ምርቶችን ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ባሉ ሀገራት እየተላኩ መሆኑን ገልጸዋል። የኢፕድ እንደዘገበው ሆርቲካልቸር ዘርፉ እንደሀገር ካለው አቅም አንጻር እስካሁን እያስገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ እምብዛም አይደለም ብለዋል አቶ አብደላ። ይህም በሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ያሳያል ብለዋል። በቀጣይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በፖሊሲ እና በስትራቴጂዎች በመደገፍ የተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!