
ባሕር ዳር: ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአዊ ብሔረሰብ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በሰጡት መግለጫ በየዓመቱ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል በጣሊያን ወረራ ጠላትን በመደምሰስ ነፃ ያወጡ ፈረሶችን ለመዘከር መኾኑን ጠቅሰዋል። በአገው ማኅበረሰብ ፈረስ ሁሉ ነገሩ ነው ብለዋል።
በአገው ሕዝብ እና ፈረስ የተለየ ቁርኝት መኖሩ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ ለ84ኛ ጊዜ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል በብሔራዊ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገበውን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
አቶ ቴዎድሮስ አያይዘውም በዓሉን በድምቀት ለማክበር የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን ጠቅሰዋል። ነዋሪው የአገውን ባሕል እና እሴት ተላብሰው እንግዳ እንዲቀበሉ እና መላው ኢትዮጵያዊያን በዕለቱ እንዲታደሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ለይኩን ሲሳይ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የተጣላን ለማስታረቅ ፍርድ ሲጓደል የሚካስበት ሥርዓት ያለበት መኾኑን ጠቁመዋል። ማኅበሩ በችግር ጊዜ ዘማች በሰላም ጊዜ አምራች መኾኑን ተናግረዋል።
ለ84ኛ ጊዜ የሚከበረው የፈረሰኞች በዓል እንዲሳካ የተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች አጋርነታቸውን እየገለጹ መኾኑን ገልጸዋል። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ሌሎች ተቋማት እና ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀመንበር ጥላዬ አየነው እንደገለፁት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በጣሊያን ወረራ ማግስት ከ30 በማይበልጡ አባላት ተመስርቶ በአሁኑ ሰዓት ከ62 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ተናግረዋል።
ማኅበሩ በቀበሌ፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ የተደራጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥላዬ ጥር 23/2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር መግለጻቸውን ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!