
አዲስ አበባ፡ ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ”ሪድ ቱ” ፕሮጀክት በሚል ዩኤስ ኤድ ለተማሪዎች ቁሳቁስ በማቅረብ ከጦርነት ሥነልቦና አንዲያገግሙ የማድረግ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ ይገኛል።
ይህንንም መሠረት በማድረግ ስዕል ከጦርነት ሥነልቦና ማገገሚያ ሁነኛ መንገድ ነው በሚል በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በነበረባቸው ሦስት ክልሎች በተማሪዎች ተስለው የተመረጡ 56 ስዕሎችን በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል የስዕል አውደርዕይ አቅርቧል።
የ”ሪድ ቱ” ፕሮጀክት ኀላፊ ጣሰው ዘውዴ (ዶ.ር) የስዕል ጥበብ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኃላ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ሥነልቦናቸው ተጎድቶ ነበር ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የሥነልቦና፣ የሙዚቃ እና የጥበባት ማገገሚያ ሥልጠና ሰለመስጠታቸው አስረድተዋል። የስዕል አውደርዕዩም የሥነ ልቦና ማገገሚያ ውጤት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ መንገድም ሕጻናትን ለማከም ጠቃሚ ኾኖ የተገኘ ነው ብለዋል።
በስዕል አውደርዕዩ በ4ኛ እና በ5ኛ ክፍል ተማሪዎች የተሳሉ የገጠር መንደሮች፣ አትሌቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሌሎች ስዕሎች ለእይታ ቀርበዋል። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሦስት ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ምክንያት እንደነበረ ተገልጿል።
በአውደርዕዩ መክፈቻ የትምህርት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ሕጻናት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!