የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የአሠራር ሥርዓት ለማዘመን የሪፎርም መመሪያ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን አስታወቀ።

15

ደሴ: ጥር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሥልጣኑ የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በኮምቦልቻ ከተማ ገምግሟል፡፡

በአማራ ክልል ከ8ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከ74 በላይ ዩኒየኖች በሥራ ላይ መኾናቸውን የክልሉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

በእነዚህ ማኅበራት እና ዩኒየኖች አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለቶች እንዳይኖሩ በማድረግ ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የባለሥልጣኑ ምክትል ኀላፊ እንዳልካቸው ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኀላፊው ባለፉት ስድስት ወራት ግን የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት ኾኖባቸው መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

በችግር ውስጥ ኾነውም ቢኾን በተለይም በከተሞች ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት በደሴ፣ በወልድያ፣ በባሕርዳር እና በደብረ ብርሃን ከተሞች ላይ የተለያዩ የገበያ ማረጋጋት ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ነው የገለጹት፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በነበረው አፈጻጸም ከቦታ ቦታ ልዩነቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ምክትል ኀላፊው የቁርጠኝነት ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት ችግሮቹን ለመፍታትም ሪፎርም አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ወቅቱ የሚጠይቀውን ተወዳዳሪነት ለማምጣት በቴክኖሎጂ እና በሠለጠነ የሰው ኀይል ለማዘመን የሪፎርም መመሪያ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት፡፡

በመመሪያዎቹ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ጠቅሰዋል፡፡ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሚኾኑበት አሠራር ይመቻቻልም ነው ያሉት፡፡

የሪፎርሙ ሥራ ተግባራዊ ሲደረግ አሁን የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል ሀሳብ እንዳላቸውም የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ትምህርት ቤት ገንብቶ አስመረቀ፡፡
Next articleየስዕል ጥበብ ተማሪዎች ከጦርነት ሥነልቦና እንዲወጡ እንደሚያግዝ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ ገለጸ።