“በግማሽ ዓመት ከሀገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደውን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ተችሏል” የገቢዎች ሚኒስቴር

11

ባሕር ዳር: ጥር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢዎች ሚኒስቴር በግማሽ ዓመት ከሀገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደውን ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን ገልጿል። ሚኒስቴሩ የታክስ ሥርዓት ዘርፍ የመጀመሪያውን የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የታክስ ሥርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ 167 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 168 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል። በዚህም የዕቅዱን 100.50 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

አፈጻጸሙ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ29 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ወይም የ21 ነጥብ 22 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከሀገር ውስጥ የዕቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት ቢቻልም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው አንጻር በታክስ አሰባሰቡ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ ይህንን ተግዳሮት ለመቅረፍ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የታክስ ሥርዓት ዘርፍ አመራሮች እየተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም የሥራ አቅጣጫም ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በከተማዋ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ትምህርት ቤት ገንብቶ አስመረቀ፡፡