“ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን አስገዳጅ ነው” አቶ ጥላሁን ደጀኔ

35

ባሕር ዳር: ጥር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ እና ሌሎች መሪዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ ምክክር ተካሂዷል። በምክክሩ የተገኙት መሪዎች የግጭት ሀሳቦችን በማርገብ ወደ ሰላማዊ ሀሳቦች ለማምጣት የተሠሩ ሥራዎች ውጤት እያመጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የፖለቲካ እና የአስተሳሰብ ችግሮች እየተስተካከሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በማወቅም ኾነ ባለመዋቅ ለግጭት ራሳቸውን ዳርገው የነበሩ ወጣቶች እየተመለሱ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

ወረዳዎች ከነበረባቸው አስቸጋሪ ችግሮች እየወጡ እንደኾነም ገልጸዋል። ሰላም አስከባሪ ኀይሎችን የማሠልጠን እና የማብቃት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የሚሊሻ እና የፖሊስ አባላት እንደገና በመደራጀት ለሕዝብ ሰላም እየሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡን የሚዘርፉት እና ማኅበረሰቡን የሚያስቸግሩ ኀይሎችን ሕዝቡ እየታገላቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል። በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የወረዳ መሪዎቹ እንዳሉት አሁንም አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይገባል። አሁንም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ መደበኛ ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚቸገሩም ገልጸዋል። የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የጸጥታ ኀይሎች በችግር ውስጥም ኾነው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። መረጃ የመስጠት እና የመቀበል ፍሰቱ እየተሻሻለ መኾኑንም አንስተዋል።

ሰላም በኾነባቸው አካባቢዎች መደበኛ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የመማር ማስተማር እና ሌሎች ሥራዎች እየተከወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የተቀናጁ ሥራዎችን በመሥራት ስጋት ያለባቸውን አከባቢዎች ሰላም ማስፈን እና መደበኛ ሥራዎችን መሥራት ይገባልም ብለዋል። በሥፋት ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች በእጅጉ እየቀነሱ መኾናቸውን መሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ሕዝብን በመያዝ አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን እና ወደ መደበኛ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ መመለስ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሕዝብ እየደረሰበት ባለው ችግር መማረሩን እና የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራለት በተደጋጋሚ እየጠየቀ መኾኑንም ተናግረዋል።

በምክክሩ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት መሪዎች ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊት መረጃዎችን ማድረስ ከቻለ እየዘረፈ እና እየሰረቀ የሚሸሸውን የታጠቀ ኀይል በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቆም ይቻላል ነው ያሉት። የአካባቢው ሰላም ከነበረበት በእጅጉ ተሻሽሏል፤ የሕዝብን ሰላምም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በዞኑ ያለው የሰላም እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን አስገዳጅ ነው፣ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ሰላም ወሳኙ ጉዳይ ነው ብለዋል። ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት የተዛባውን አስተሳሰብ ማረም እና ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።

ሕዝቡ የተዛቡ አስተሳሰቦች እንዲታረሙ እና ሰላም እንዲሰፍን እየጠየቀ እና ከመንግሥት ጎን እየቆመ መኾኑንም አመላክተዋል። በተደረገው የሰላም ጥሪ በርካታ ታጣቂዎች ለሰላም መግባታቸውንም ገልጸዋል።

ለመከላከያ እና ለሌሎች የጸጥታ ኀይሎች የነበረው የተዛባ አመለካከት በእጅጉ እየተሻሻለ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር የሚቆመው በየጊዜው እየበዛ መሄዱንም አመላክተዋል። የፖለቲካ መሪዎች ከሕዝብ ጋር እየተገናኙ ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡት ውይይቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል። የውስጥ አቅምን በማጠናከር እና በማሠባሠብ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይገባልም ብለዋል። የሰላም አስከባሪ ኀይሎችን በማብቃት ሕዝብን የሚያማርሩ አካሄዶችን መግታት እና ማረም ይገባል ነው ያሉት።

ያሉ ክፍተቶችን በማረም የዞኑን ሰላም ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል። በየጊዜው በሚሠሩ ሥራዎች ላይ በመወያየት የጋራ አቋም መያዝ ይገባል ብለዋል። በተቀናጀ አግባብ መሥራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዞኑን ሙሉ ሰላማዊ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ተልእኮውን በማይፈጽም መሪ ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱም አመላክተዋል። እስካሁንም እርምጃ ሲወስዱ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት። ሕዝቡ ያጣውን ሰላም በመመለስ ዞኑን የሰላም እና የልማት ቀጣና ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሲቪል የማኅበረሰብ ድርጅቶችን ማጠናከር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ።
Next article“በከተማዋ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ