
ባሕር ዳር: ጥር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቬልት ሀንገር ሂልፋ የተሰኘ የጀርመን በጎ አድራጊ ድርጅት በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ በአማራ ክልል ለሚያከናወነው የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የፕሮጀክት ትውውቅ አድርጓል።
ቬልት ሀንገር ሂልፋ (ጀርመን አግሮ አክሽን) የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ትርንጎ ክንፈገብርኤል የድርጅታቸው ፕሮጀክት ዓላማ በአማራ ክልል የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገለግሉ ሲቪል ማኅበራትን አቅም በመገንባት ማገዝ መኾኑን ገልጸዋል።
የድጋፍና የአቅም ግንባታ አግኝተው የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ እና ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ማገዝ መኾኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት እና ኅብረተሰብ ግንኙነቶች በምክክር መብት እና ግዴታን በመወጣት ላይ የተመሰረተ እንዲኾንም ግንዛቤ ይፈጠራል፤ ክልሉ ያለበትን ወቅታዊ ችግር ለመቅረፍም አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ማኅበረሰብ ኅብረት ዳይሬክተር ንጋቱ ደስታ ፕሮጀክቱ በክልሉ ለሚገኙ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።
በመኾኑም በክልሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተሳትፎ የሚፈልጉ የሰላም እጦት እና የድርቅ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥቅም አለውም ብለዋል።
ኅብረተሰቡም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በግንዛቤ ፈጠራ፣ በሰላም ማስፈን ተጠቃሚ እንደሚኾን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን የፕሮጀክት ትውውቁ ከገንዘብ ቢሮ ጋር መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መንግሥት በመመካከር የማኅበረሰብ ችግርችን የመፍታት ዓላማ እንዳለው ጠቁመዋል። የመልካም አሥተዳደር፣ የልማት እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችም አብረው ይሠራሉ ነው ያሉት።
የሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባሕል እና ልምዱን ዐውቀው ስለሚሠሩ ለውጤታማነቱ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ይዞት የመጣው ሃብት በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ እና የአጋር አካላትን ድጋፍ ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደ ትልቅ አጋጣሚ ይኾናል። ከሰላም አኳያም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለአቅም ግንባታ ሥራ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ይጠበቃል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ዋሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!