“ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል” የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት

35

ባሕር ዳር: ጥር 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

እንደ ሀገር ሰንደቅ የሚቆጠረው ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ኢትዮጵያውያን የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው እንዲሁም በጉልበታቸው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህን ተከትሎ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል።

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከኅብረተሰቡ ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ከኅብረተሰቡ 625 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ503 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ገቢው ከተሰበሰበባቸው መንገዶች ውስጥ ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከፒን ሽያጭ እና 8100 ኤ በአጭር የሞባይል የጽሁፍ መልእክት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ በክልሎች የሚደረገው የድጋፍ ስራ ወጥ አለመሆን ግቡን ለማሳካት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል ። ኢትዮጵያ የወጠነችውን የልማት ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው፡፡
Next articleኢትዮ ቴሌኮም በ6 ወር የሥራ አፈጻጸም ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።