
ባሕር ዳር፡ ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጣና ዳር ፈርጧ ውቧ ከተማችን ባሕርዳር ከጥር 10 እስከ14/2016 ዓ.ም ” የከተራ፣ የጥምቀት ፣የቃና ዘገሊላና አቡነ ዘርዓ ብሩክ” በዓላት መንፈሳዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በመከበራቸው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለመላው ማኅበረሰብ ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና እንዳላቸው ገልጸዋል ።
አቶ ጎሹ እንዳላማው ባስተላለፉት የምስጋና መልዕክታቸው እንደገለፁት ባሕር ዳር በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ገፀ-በረከቶች የከበረች ውብ ለኑሮም ይሁን ለሥራ እንዲሁም ለቱሪዝም መናገሻነት ምቹ የሆነች ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። ይህንን ተከትሎ ከተማዋ በባሕልና በታሪክ የበለፀጉ ብርቅየ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩባት በመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በየጊዜው የበዓሉ ታዳሚ መሆናቸው የማይታለፍ ሀቅ ስለሆነ ይህን ዝግጅት ከጅማሬ እስከ ፍፃሜው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ስኬታማ ሆኗል ብለዋል።
በዚህም በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ለብፅዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ፣ የሰሜን ጎጃምና የባሕር ዳር አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፣ለገዳማትና አድባራት አሥተዳዳሪዎች፣ ለሠንበት ትምህርት ቤቶችና ለማህበረ ቅዱሳን አባላት፣ ለሠላም ወዳዱና አርቆ አሳቢው የከተማችንና አካባቢው ማኅበረሰብ ፣ለእንቁ የከተማችን ወጣቶች ፣ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎችና ከውጭ ሀገራት በዓልን ከእኛ ጋር ለማሳለፍ መርጠውን ለመጡ ቱሪስቶች፣ከመላው የፀጥታ መዋቅር ጋር በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ድባቡን እንደጠበቀ እንዲከበርና በዓሉን ለማክበር የወጣው ሕዝበ ክርስቲያን በሰላም አከናውኖ በረከት እንዲጎናፀፍ በማድረግ በኩል ላደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረት በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም የላቀ ምስጋና ሳቀርብ በታላቅ ደስታ ውስጥ ሆኘ ነው በማለት የምስጋና መለዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ስለሆነም በቀጣይ በአደባባይ ለማክበር በታላቅ ጉጉት የምንጠብቃቸው በዓላት “የሠባር ጊዩርጊስና የጥርን በባሕርዳር ኩነቶች” ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ሕዝባችን እንዲሁም ለቱሪስት እንግዶቻችን የሃይማኖት ፣የባሕልና የታሪክ ኩነትን በማሳየት ከፍተኛ መስተጋብር የምንፈጥርባቸው ዋነኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈርጥ በመሆናቸው እንደሰሞኑ ሁሉ በቀጣይ የሚከበሩ የሰባሩ ጊዮርጊስ ፣የአስተርዮ ማርያም ፣ የጀልባና ታንኳ ቀዘፋ ውድድሮችንና መሰል ኩነቶችን በጋራ ሆነን በማክበር ያለምንም የፀጥታ ስጋት የበዓሉን አውድ ብቻ በማሰብና በማከናወን ምእመኑ በነፃነት ማክበር እንዲችል በማድረግ የየድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!