የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምሮች ለኢኮኖሚ ልማት እና እድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ሲል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አስታወቀ።

35

ባሕር ዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምርምሮች ለኢኮኖሚ ልማት እና እድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገልጸዋል።

በስድስት ወራት ብቻ በዘርፉ አሥር የተለያዩ የምርምር ሥራዎች የተደገፉ ሲሆን በጤና፣ በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሠሩ ስድስት የምርምር ውጤቶችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በመሆኑም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአምስቱ የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ተደርጎ በስፋት እየተሠራበት ይገኛል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምርምሮች ለኢኮኖሚ ልማትና እድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ሀገራዊ የምርምር ሥነ ምኅዳር በዘመናዊ አሠራር እና ቴክኖሎጂ እንዲመራ ሚኒስቴሩ በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ የተደገፉ የምርምር ሥራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ውጤታማ የሆኑትን በማስቀጠል ወደ ኋላ የቀሩትን ደግሞ እየደገፈና እያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከአጋር አካላት በተገኙ ድጋፎች ምርምሮች መደገፍ መቻላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በተገኘ ድጋፍ አሥር የተለያዩ ምርምሮች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

“አክትስ” ከተባለ ተቋም ጋር በተደረገ የጋራ ሥራ በተገኘ 250 ሺህ ዶላር ድጋፍም በጤና፣ በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሠሩ ስድስት የምርምር ውጤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በዘጠኝ ክልሎች የሳይንስ ካፌዎችን መገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ወጣቶች ልምድ እና እውቀቶችን እንዲጋሩ እንዲሁም የሳይንስ እና የኢኖቬሽን ባሕል እንዲዳብር የሚያደርግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአይሲቲ ፓርክ የኮሪያ መንግሥት ባደረገው ሦስት ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጀማሪዎች ፈጠራቸውን የሚያዳብሩበት ዘመናዊ ማዕከል ወይም የኢንኩቤሽን ማዕከል ተገንብቶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ተመርቆ ማዕከሉ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፤ ጀማሪዎች ልምምድ የሚያደርጉበት እና የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያዳብሩበት ይሆናል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በድል ያጠናቀቀችበት ታሪክ የማይረሳው ቀን – ጥር 13/1954 ዓ.ም
Next articleለውጪ ገበያ ከተላኩ የቁም እንስሣት ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ።