
ባሕር ዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሚቀጥሉት አስር ቀናት በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እና የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
እንደ ኢንስቲትዩቱ መግለጫ በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ፣ በምስራቅ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው እርጥበት የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለእንስሳት የግጦሽ ሳር እና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲሁም ለሰብሎች እና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የሚኖረው እርጥበት ለማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራትም የሚጠቅም በመሆኑም አስፈላጊው እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
በዚሁ ወቅት የላይኛው እና መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣ አፋር ደናክል፣ የመካከለኛው እና ምስራቃዊ ዓባይ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋ እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!