
እንጅባራ ፡ ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የ2016 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራን ለማስጀመር የሚያግዝ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በቻግኒ ከተማ አካሂዷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መቀነስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት የሚሉ ዘላቂ ግቦችን አንግቦ ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ኅብረተሰቡን ከተፈጥሮ ጋር ይበልጥ አቆራኝቶታል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በተሠሩ ሥራዎችም በአፈር ለምነት ላይ ከተገኙ ለውጦች ባሻገር የብሔረሰብ አሥተዳደሩን የደን ሽፋን ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲል እገዛ ማድረጉን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ሥራ ባለፉት ዓመታት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት እና የነበሩ ድክመቶችን በማረም ወጥነት ባለው መልኩ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉንም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፤ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በተቀናጀ አብሮነት እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህን በልዩ ትኩረት የሚፈጸም ተግባር መኾኑን ተናግረዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎችም የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ የቦታ እና የሰው ኀይል ልየታ እንዲሁም የማልሚያ መሣሪያዎች ዝግጅት በማጠናቀቅ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጥር 15/2016 ዓ.ም በይፋ በሚጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ 310 ተፋሰሶች በነባርና በአዲስ የሚለሙ ሲኾን ከ125 ሺህ በላይ የሰው ኀይል በሥራው እንደሚሳተፍም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!