
ጎንደር፡ ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ጎንደር ታምርት፤ ያመረተችውን ትጠቀም” በሚል መሪ ቃል የባለሃብቶች ፎረም በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ አማረ በከተማዋ እና በአካባቢው ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ እንደ ክልልም የሃብት ልየታ በማድረግ ጥናት መደረጉን ያነሱት አቶ ዮሐንስ እነዚህን ሃብቶች ለመጠቀም የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ሂደትና ማነቆዎችን የመፍታት ሂደት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ኢንቨስትመንት ሰላም ይፈልጋል ያሉት አቶ አማረ በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያሉ ባለሃብቶችም ይሁኑ ማኅበረሰቡ ለሰላም ሊሠራ ይገባል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ ጎንደር በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ አቅም ያላት ከተማ በመኾኗ ለአምራቹ ምቹ ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲኖረው ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ በአምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች 201 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ በቅድመ ግንባታ 25፣ በግንባታ ላይ ያሉ 58 ፣ግንባታ ያጠናቀቁ እና በማጠናቀቅ ላይ ያሉ 70፣ ምርት ላይ ያሉ 48 ፕሮጀክቶች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ 31 የሚኾኑት በዲያስፖራ ማኅበረሰቡ እየለሙ የሚገኙ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በመድረኩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ በከተማዋ እና በዙሪያው የሚገኙ ሃብቶችን በማጥናት ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
በመድረኩ በከተማዋ የሚገኙ አልሚ ባለሃብቶች እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!