
ባሕር ዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የ28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ውሳኔዎችን ለመተግበር ከሁሉም አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አዘጋጅነት በዱባይ ከተማ ካለፈው ኀዳር 30 እስከ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም ድረስ የተካሄደውን 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
በማብራሪያውም ኢትዮጵያ በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) በዝርዝር በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች እንዲሁም ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ባሉ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ፕሮጀክቶች ተያያዥ ጉዳዮች ስኬታማ ተሳትፎ አድርጋ መመለሷን አስታውሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተሳተፉበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ሀገሪቷን እየገጠሙ ለሚገኙ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን እንዳሳወቁ ጠቅሷል፡፡
በስንዴ ምርት፣ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ በምግብ ራስን ለመቻል የተወጠነው የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ አማራጭ የትራንስፖርት ዘርፎች ማበረታቻ የተወሰዱ እርምጃዎችን በዝርዝር እንዳስረዱም ሚኒስቴሩ አስረድቷል፡፡
ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች በእዳ መቆለል የተነሳ ከፍተኛ ተግዳሮት እየገጠማቸው መኾኑን ጠቅሰው የሚመለከታቸው ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተገቢ ማሻሻያ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም መግለጫው አስታውሷል፡፡
የአየር ንብረት ተጽዕኖ ተጋጭነትን በትብብር ስለመፍታት፣ ፍትሐዊ ፣ ተመጣጣኝ፣ ተደራሽ እና ሥርዓት ያለው የኢነርጂ ሽግግር እና የቡድን 77 እና የቻይና ጉባኤ በሚመለከታቸው የዘርፉ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ተሳትፎ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ሁሉን ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን አቋም እና ሀሳብ ማጋራት እንደተቻለ ነው የተገለጸው፡፡ በጉባኤው ወቅት ኢትዮጵያ “ዩ ኤ ኢ ዔ ኤም ኢ ዔ ፖወር” ከተሰኘ ድርጅት ጋር በ600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የ300 ሜጋ ዋት የንፋስ ኀይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሁም ከጣሊያን የ8 ሚሊዮን ዩሮ የአካባቢ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት ስምምነት መፈራረሟ ተመላክቷል፡፡
በ28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ በመሪነት እንደተሳተፈች የገለጸው ሚኒስቴሩ አባል በኾነችባቸው የአፍሪካ ቡድን፣ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ቡድን በመምራትም መሳተፏን አስታውቋል፡፡
በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ ፕሬዚዳንት እንደመኾኗ በጉባኤው አፍሪካውያን በአንድ ድምጽ እንዲደራደሩ እና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ አስተባብራለች ተብሏል፡፡
በጉባኤው ወቅት የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የሚውል የ792 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጥፋት እና ውድመት ፈንድን ጨምሮ 85 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመስጠትም ቃል እንደገቡ ተጠቁሟል፡፡
የዓለም ባንክ በበኩሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተያያዥ ለኾኑ ፕሮጀክቶች በ2024 እና 2025 የ9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ የባለብዙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ድጋፎች ከ22 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ በጀት ለመመደብ ቃል ገብተዋል ነው የተባለው፡፡
በኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ያሉትን ራዕዮች እና አሁን እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችን በኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ፓቪሎን በኤግዝቢሽን መልኩ እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በተመድ ማዕቀፍ በባለብዙ የትብብር ማዕቀፎች ያላትን እምነት መሰረት በማድረግ የ28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ውሳኔዎችን ለመተግበር እና በትግበራ ሂደት ከሁሉም አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኗንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!