
ባሕር ዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተገቢው የዲፕሎማሲ መንገድ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና በዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ተናገሩ።
አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የማንንም አካል የማይጎዳና በሰጥቶ መቀበል መርህ የተቃኘ ነው ብለዋል፡፡ ራስን ለመጠበቅና ትብብርን ለማጠናከር የባሕር በር ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሩ በዚህ አግባብ በተገቢው ዲፕሎማሲ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር የማግኘት መብት እንደኾነ አስረድተዋል።
አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) በተገቢው ጥንቃቄ እና ብቃት ባለው ዲፕሎማሲ እየተመራ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ሕዝብ ይዞ የባሕር በር የሌለው ሀገር በዓለም እንደሌለ ያስታወሱት ኢንጂነር ስለሺ፤ በቀጣይ ስድስት ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ 150 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ትንበያ መኖሩን አመላክተዋል።
የሕዝብ ቁጥሩ ከዓለም ዘጠነኛ ያደርገናል ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህ ሰፊ ሕዝብና እያደገ የሚመጣውን ኢኮኖሚ በአግባቡ ለማስተናገድ ወደብ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ከእኛ የባሕር በር ፍላጎት አኳያ በተጻጻሪው የሚቆሙ ሀገሮች ኢትዮጵያ ወደብ በማግኘቷ ተጎድተው ሳይሆን የኢትዮጵያን ማደግ በበጎ ስለማይመለከቱት የሚመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ አቅሟን እያጠናከረችና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን እያጎለበተች ከመጣች ስጋት ስለሚሰማቸው ባለችበት እንድትቆም የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ ግልጽ ነው።
ኢትዮጵያን የሚጻረሩ ሀገራት ይታወቃሉ፤ እነሱ ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት አለብን። የተጻራሪዎቻችንን ልክ በሚመጥን መልኩ ምላሽ በመስጠትና በመመከት የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት በአግባቡ ማሳካት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን የባሕር በር ስምምነት ተከትሎ ጉዳዩን ከሶማሊያ ጋር ውጥረት ውስጥ ለመክተት የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ እየተጓዘች የባሕር በር ተከልክላ ሠላማዊ የሆነ ቀጣና ሊኖር እንደማይችል የተናገሩት አምባሳደሩ፤ በጋራ ትብብር ላይ የተመሠረተ ልማትና ዕድገት ለቀጣናው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ለማሳደግ እንዴት አድርገን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትብብር መፍጠር ይገባል የሚለው ላይ ማተኮር እንጂ የኢትዮጵያን ፍላጎት ብቻ መቃወም ተገቢ አይደለም ሲሉም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን በሕዝቦች መካከል በሚደረግ የጋራ መግባባት፣ በመሪዎች የትብብር መንፈስና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ አግባብ ማልማት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አምባሳደር ስለሺ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎትና ተጠቃሚነት በአብሮ የመሥራት መንፈስ ላይ የተመረኮዘና ለጋራ ዕድገት የሚበጅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
