
ባሕር ዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አልማዝ ጊዜው (ዶ.ር) እንደገለጹት በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በ201 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደን፣ የፍራፍሬ እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል። ችግኞች በ84 ሺህ ጣቢያዎች ላይ እየተዘጋጁ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በ2016 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ጠቅሰዋል። በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
የአፈር እና ጥበቃ ሥራ በተሠሩባቸው አካባቢዎች የአትክልት እና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል። 20 በመቶዎቹ ሀገር በቀል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከ70 በመቶ በላይ የተከላ ቦታዎች መለየታቸውን ገለጸዋል የምክትል ኃላፊዋ። ክልሉ ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዝግጅቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት በክልሉ የተተከሉ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በ2015 ዓ.ም የክረምት ወቅት ከተተከሉ ችግኞች 84 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ በችግኝ ተከላ ወቅት ያሳየውን ተሳትፎ በማሳደግ የችግኝ እንክብካቤውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔያቸው በደቡብ ጎንደር ሁለት ወረዳዎች፣ በሰሜን ወሎ አምስት ወረዳዎች እና በዋግኽምራ አካባቢዎች አነስተኛ ነው ያሉት ዶክተር አልማዝ ችግሩን ለመቅረፍ ችግኞችን ከማዘጋጀት እስከ እንክብካቤው ያለውን የተቀናጀ ሥራ በሥልጠና መልክ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለችግኝ ተከላው የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት፣ የግብዓት ማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የችግኝ ፕላስቲኮች እና ከ200 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ኮምፖስት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ በርካታ ተራራዎች የሚገኙ በመሆኑ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ከዓመት እስከ ዓመት የሚሠራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አልማዝ በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ አጠናክሮ ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል። በመጨረሻም ለአረንጓዴ ዐሻራ ሥራው ውጤታማነት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!