
ባሕር ዳር: ጥር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት አከባበር ቀመር መሠረት ከበዓለ ልደት፣ ግዝረት እና ጥምቀት ቀጥሎ ቃና ዘገሊላ በድምቀት ይከበራል፡፡ ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ያሉት ቀናት በኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ዘንድ አይረሴ የሚባሉ ናቸው፡፡ ከሕጻናት እስከ እመበለት፤ ከወጣት እስከ አዛውንት በወግ በወጉ የሚደሰቱባቸው ቀናት ኾነው ያልፋሉ፡፡
በከተራ በዓል ታቦታት ከመንበራቸው በክብር እና አጀብ ወጥተው በወንዝ ዳር ያርፋሉ፡፡ ካህናት በሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ አበው በምሥጋና፣ እናቶች በእልልታ እና ወጣቶች በሆታ ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ያደርሳሉ፡፡
ድንኳን ለታቦታቱ እና ዳስ ለካህናቱ በምዕመኑ ይዘጋጃል፡፡ ከባሕር ወደ የብስ በሚነፍስበት በዚያ ሌሊት ምዕመናኑ ታቦታቱን ከብበው ብርዱን እና ቁሩን ተቋቁመው ሌሊቱን በዚያ ያሳልፋሉ፡፡ ከንጋት ቅዳሴ ቀጥሎም ጥምቀት በካህናት ለምዕመናኑ ይሰጣል፡፡
ጥር 11 ከእኩለ ቀን ጀምሮ ታቦታት ካረፉበት ጥምቀተ ባሕር ተነስተው ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ፡፡ በጥምቀት በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትዕይንቶች ይስተናገዳሉ፡፡ “ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዲሉ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው ለጥምቀት የማይገለጥ ውበት፤ የማይስተዋል ጀግንነት የለም፡፡ ጥምቀት በኢትዮጵያዊያን ምድር ሁሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይኸ ሃይማኖታዊ በዓል በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ልዩ ስፍራ ባሕላዊ ፋይዳውም የጎላ ነው፡፡
ከጥምቀት በኋላ ያለው በዓል ቃና ዘገሊላ ይባላል፡፡ በዚህም ቀን ግን የጥምቀት በዓል አለ፡፡ እንደሌሎቹ ታቦታት በከተራ በዓል ወደ ጥምቀተ ባሕር የወረደው የቅዱስ ሚካኤል ታቦት በጥምቀት እለት ወደ መንበሩ አይመለስም፡፡ “በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት” እንዲሉ ክርስቲያኖች የቅዱስ ሚካኤል ታቦት በጥምቀተ ባሕሩ ሁለት ቀናትን ቆይቶ በቃና ዘ ገሊላ ወደ መንበሩ ይመለሳል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ሆነ” ይለናል፡፡ ክርስቲያኖች ደግሞ ምን በኾነ በሦስተኛው ቀን? ሲሉ ያጠይቃሉ ይሉናል በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የሊቃውንት ጉባኤ ሠብሣቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ፡፡ መዋዕለ ጾሙን የካቲት 20 ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ገሊላ አውራጃ ቃና በተባለች መንደር ሰርግ ኾነ፡፡
መምህሩ እንደሚሉት በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዩሃንስ እጅ የተጠመቀው ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆረንጦስ ከ40 ቀን ጾም እና ጸሎት በኋላ መለኮታዊ ሥራውን የጀመረው በቃና ዘገሊላ በሰርግ ቤት ውስጥ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመቀየር ነበር፡፡ በዚህ ሰርግ ብዙ ሰዎች የታደሙ መኾኑን የወይን ጠጁ ማለቅ ያስረዳል፡፡ በእርግጥም የተጠሩት ሰዎች ብዙ ቢኾኑም ብዙዎችን መመገብ የሚችል አምላክ በሰርግ ቤት መጠራቱ ግን ሰርጉን ልዩ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
“የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር መቀናጀት አለበት” በማለት የቃና ዘ ገሊላ በዓል ከጥምቀት በዓል ማግስት ይከበራል የሚሉት መምህሩ በዚህ በዓል ክርስቶስ የኾነ እርሱ ኢየሱስ “ጌትነቱን ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” እንደተባለ በተዓምራቱ መጀመሪያ ሐዋሪያት ጌትነቱን ተረዱ ይሉናል፡፡
“ቃና ዘ ገሊላ ምሥጢር ነው፡፡ ሚዜ ሙሽራውን የሚያጠምቅበት፤ ሚዜ አሳላፊ የሚኾንበት” ያሉን ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ በሰርጉ ቦታ የወይን ጠጅ አልቆባቸው አሳላፊዎች ሲጨነቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስድስት የድንጋይ ጋን ውኃን ወደ ወይን ጠጅ ቀይሮላቸዋል ነው ያሉን፡፡ “አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን አቆይተሃል” እንዳለ መጽሐፍ፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
