
ባሕር ዳር: ጥር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥምቀት ቀጥሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበረው የቃና ዘገሊላ ሃይማኖታዊ ክዋኔ በጎንደር ከተማ ውስጥ በተለየ ድምቀት እየተከበረ ነው።
የከተራ ቀን ወደቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የወረዱ ታቦታት ትላንት ሥርዓተ ጥምቀቱ ከተፈጸመ በኃላ ወደ መንበራቸው ገብተዋል።
በጃን ተከል ዋርካ አካባቢ የሚገኘው የአጣጣሚ ሚካኤል ደብር ታቦት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚያዝዘው መሰረት እዚያው በባሕረ ጥምቀቱ ለሁለተኛ ቀን አድሮ ነው ዛሬ ወደ መንበሩ የሚገባው።
አሁን ላይ ታቦቱ በቀሳውስት ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ በሰንበት ተማሪዎች የቃና ዘገሊላ ልዩ ዝማሬ፣ በእናቶች ልዩ እልልታና ጭብጨባ እንዲሁም በወጣቶች ሆታ ወደ መንበሩ እየተመለሰ ነው።
ታቦቱ ወደ ደብሩ ለመግባት በሚደረገው ጉዞ ከፒያሳ አጼ ቴዎድሮስ ሐውልት ጀምሮ መስቀል አደባባይ እና ጃን ተከል ዋርካ አካባቢ ድረስ “የጠጠር መጣያ የለም” በሚባልለት የምዕመናን አጀብ እየተጓዘ ነው።
“በሕይወት ግባ በሕይወት፣
የሀገራችን ታቦት…..በጉዞው ላይ ጎልቶ የሚሰማ ዝማሬ ነው።
እንኳን ለቃና ዘገሊላ ዓመታዊ በዓል አደረሳችሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!