“ብዙ አማራጮች ሳሉት እርሱ ግን በውኃ ተጠመቀ”

36

ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ፣ በወልድ ውሉድ የኾኑ እና በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊያን የተሰኙ ክርስቲያኖች ልጅነትን ያገኙ ዘንድ ይጠመቃሉ፡፡ ጥምቀት እንደገና መወለድ ነው ብለው በሚያምኑት ክርስቲያኖች ዘንድ ውኃ እና ጥምቀት የተለየ ፍቅር እና ትስስር አላቸው፡፡

በጥምቀት ታቦታት ስለምን ውኃ ወዳለበት ወንዝ ወርደው ያድራሉ፤ ክርስቶስ ኢየሱስስ ስልምን በውኃ ተጠመቀ? ለሚለው ጥያቄ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መልስ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መምህር የኾኑት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ዓለማየሁ “ጥምቀት” ሲባል በጥቅሉ ትንታኔ ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡

ማንኛውም ሰው ክርስትና ተነስቶ ክርስቲያን ሊባል እና ሊኾን ሲመጣ ካህኑ ውኃውን ባርኮ ወደ ማየ ገቦ ይቀይረዋል የሚሉት መምህሩ ይህም በ40 እና 80 ቀናት ውስጥ ልጅነት የሚገኝበት ክርስቲያናዊ ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡

ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት መካከል ምስጢረ ጥምቀት አንዱ እንደኾነ የሚያነሱት መምህሩ ወንዶች በ40 ቀናቸው እና ሴቶች በ80 ቀናቸው ተጠምቀው ጸጋ ልጅነትን ያገኛሉ ነው ያሉት፡፡ ይህን መሰሉ ጥምቀት ምስጢረ ጥምቀት ይባላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በባሕረ ጥምቀት እና በጸበል የምናገኘው ጥምቀት ማየ በረከት ይባላል የሚሉት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ካህኑ በጸሎት ወኃውን ወደ ማየ ፈውስነት ይቀይረዋል ይላሉ፡፡ መምህሩ እንደሚሉት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፡ 9 ላይ “ዐይነ ስውሩን ጭቃ ቀብቶ ሂድና በሰሊሆም ውኃ ታጠብ ሲለው፤ የሰሌሆም ውኃ የተለየ ኀይል እና ፈውስ እንዳለው እየነገረን ነው” ይላሉ፡፡

እናም ጥምቀት ሲባል አንድም ጸጋ ልጅነትን አግኝተን በክርስቶስ ክርስቲያን እንባል ዘንድ የምንወስደው ምስጢራዊ ጥምቀት፤ በሌላ በኩል ፈውስ እና በረከት እናገኝ ዘንድ የምንጠመቀው ማየ በረከት እንደኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ጥምቀት ሰፋ ያለ ምስጢር ያለው ሥርዓት ቢኾንም ዛሬ ክርስቲያኖች የምናከብረው የጥምቀት በዓል ከሞት ወደ ድኅነት፤ ከጥፋት ወደ በረከት የተሸጋገርንበት ነው ብለዋል፡፡

ውኃ ከአራቱ ባህሪያተ ስጋ መካከል አንዱ ነው የሚሉት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ዓለማየሁ “ምድርን ከውኃ ላይ ፈጠራት፤ በውኃ ላይም አፀናት” እንዲል ጥምቀቱን ለጥምቀታችን ሲል በውኃ አጸናው ነው ያሉት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ጠቅሰው መምህሩ እንደሚሉት ሴቶችም፣ ወንዶችም፣ ድሆችም ባለጸጎችም፣ ሕጻናትም፣ አዛውንትም ይጠመቁ ዘንድ ሲፈቅድ ብዙ አማራጮች ሳሉት እርሱ ግን በውኃ ተጠመቀ” ይላሉ፡፡

በውኃ መጠመቁ የድሆች አባት እና የፍትሕ አምላክ ስለመኾኑ ማሳያ ነው የሚሉት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ዋጋ ባለው ነገር ተጠምቆ ቢኾን ኖሮ ጥምቀትን የሚያገኙት ስንቶች ነበሩ ሲሉም ያጠይቃሉ፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ለሰዎች ይህንን በማድረጋችንም ፈጣሪያችን እንመስለዋለን” ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ
Next articleቃና ዘገሊላ በጎንደር በልዩ ድምቀት እየተከበረ ነው።