
ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት እና ትውፊት መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በዓል በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ይከበራል። የ2016 ዓ.ም የጥምቀት በዓልም በሃይማኖቱ ሥርዓት እና ትውፊት መሠረት በየቤተክርስቲያናቱ እና በየአድባራቱ ይከበራል።
ለመኾኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተጠመቀ? እንዴትስ ተጠመቀ? ሰዎች በተወለዱ በ40 እና በ80 ቀናቸው የመጠመቃቸው ምክንያትስ? ዓለሙስ ከጥምቀቱ ታሪክ እና ኑባሬ ምን ይማር ሲል አሚኮ የሃይማኖቱ አባትን ጠይቀዋል።
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የሊቃውንት ጉባኤ ሠብሣቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ ማብራሪያ ሰጥተውናል። ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስትን ሲተረጉም “ያችኛዋን ዘግቶ ይቺኛዋን ከፈተ” እንዳለው የብሉይ ኪዳንን ጥምቀት ዘግቶ የሀዲስ ኪዳንን ጥምቀት ለመክፈት እና ለመባረክ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቁን ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ በምክንያትነት ያነሳሉ።
”ጌታ ያልጀመረው በጎ ሥራ የለም” ያሉት ሊቁ ጥምቀትንም ክርስቶስ ራሱ ጀምሮ ማስጀመሩን ተናግረዋል። ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ስድስት እስከ ዘጠኝ ድረስ ያለውን ቃል የጠቀሱት መምህሩ በዘመኑ ዓለም በውኃ ጠፍቶ እንደነበር እና ሰዎችም ውኃ ለጥፋት እንደሚውል ያስቡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ያን ሃሳብ ለውጦ ውኃ ለዘለዓለም ህይወት እንደሚያበቃ እና ”ያመነ የተጠመቀ ይድናልን” ለማዘከር፤ የውኃን ቅድስና ለማረጋገጥ እና ውኃዎችንም ለመባረክ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ሌላኛው ምክንያት መኾኑን አብራርተዋል።
ሰው ወደ ጽድቅ መግባት የሚጀምረው በጥምቀት ስለኾነ ኢየሱስም ጥምቀትን መጀመሩን ነው የገለጹት። ”እኛ የምንጠመቀው ከእግዚአብሔር ለመወለድ ነው፤ ክርስቶስ ግን የተጠመቀው ጥምቀትን ለኛ የተባረከች ለማድረግ ነው” በማለት የክርስቶስን ጥንተ የእግዚአብሔር አብ ልጅነት አስታውሰዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ሲዘከር የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ሥራ እና ቅድስና እንደሚጠቀስ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ ገልጸዋል። በዚያ ዘመን ዮሐንስ መጥምቁ በብዛት ያጠምቅ እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እየቀረቡ ሐጢአታቸውን እየተናዘዙ ንስሐ እየገቡ የማጥመቅ ልማድ እንደነበረው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ መጠቀሱን ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠመቁ ከመጡት ሰዎች ጋር ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ከቁጥር 16 ጀምሮ እንደተጠቀሰም ገልጸዋል። ጥር 10 ቀን ለ11 አጥቢያ መጥምቁ ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው ወንዝ አቅራቢያ ከሕዝቡ ጋር ተሰልፎ ወረፋ ሲጠብቅ ማደሩን ሊቁ ጠቅሰዋል።
ከንጋቱ 10 ሰዓት አካባቢ የክርስቶስ ተራው እንደደረሰው እና ሁሉም ከተጠመቁ በኋላ ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ ቀረበ። ጌታ የሚጠመቅበት ውኃም ዮርዳኖስ መኾኑን እና ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ መኖሩን ከዮሐንስ በስተቀር ማንም አላወቀም ነበር።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ ዮሐንስ መጥምቁ ለሕዝቡ ‘በእናንተ መካከል እናንተ የማታውቁት አለ፤ ከኔ በፊት የነበረ ግን ከኔ በኋላ የሚመጣ ነው’ ብሎ እንደተናገረ መጠቀሱን መምህሩ አብራርተዋል።
ከሐጢአተኞች እንደ አንዱ ስለተቆጠረ ከሐጢአተኞች እና ንስሃ ከሚገቡት ጋራ አብሮ ተሰልፎ ቢያድርም ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ መምጣቱ የሚጠመቀው ጥምቀት የሃዲስ ኪዳን እንጂ የብሉይ አለመኾኑን ያመላክታል ብለዋል። ”ሕጓ ለብቻዋ የምትሠራ እና ለብሉይ ኪዳን ፍጻሜ የምትኾን ስለነበረች ነው፤ ተቀላቅላ የምትሠራ ሕግ አይደለችምና” ብለዋል።
ዮሐንስ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ መሄዳቸው፣ ከደረሱ በኋላም የዮርዳኖስ ባሕር መሸሿ እና የላይኛው ውኃም ተገድቦ የመቆሙ ታምር መከሰቱን ሊቀ ሊቃውንቱ ጠቅሰዋል። ይህ የአበው ሐጢአት አርቆ ትውልዱንም ከሐጢአት ነጻ ማድረጉ የታየበት እና ለዚያ ምስክር እንዲኾን የተቀመጠ ነው ብለዋል።
ዮሐንስም ሌሎቹን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን ግን በማን ስም ላጥምቅህ? ሲለው ኢየሱስ ክርስቶስም የዓለሙን ሁሉ ሐጢአት ያስተሰረየ የእግዚአብሔር በግ እያልክ አጥምቀኝ አለው።
ዮሐንስም ኢየሱስ እንዳዘዘው አጠመቀው። በዚህ ጊዜ አብ ይህ የምወደው ልጄ ነው ሲል በደመና ኾኖ መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ወረደ። እንደዚህም ኾኖ አንድነትም ሦስትነትም በዚያ ቀን ተገልጦልናል ብለን እናምናለን ብለዋል።
ክርስቶስ በ30 ዓመቱ የተጠመቀው አዳም ጥፋቱን የሠራው በ30 ዓመቱ ስለነበረ ነው። አዳም ሐጢአትን በሠራበት ዓመት ክርስቶስ ደግሞ ጽድቅን ጀመራት። ሰው ወደ ጽድቅ መግባት የሚጀምረው በጥምቀት ስለኾነ ኢየሱስም ጥምቀትን በ30 ዓመቱ ጀምሯል።
ክርስቶስ የተጠመቀው ጥምቀትን ለመመስረት ነው። የሰው ልጅ ግን የሚጠመቀው የክርስቶስን ልጅነት ለማግኘት ነው። አዳም እና ሔዋን መጀመሪያ ልጅነት የተቀበሉት በተፈጠሩ በ40 እና በ80 ቀናቸው ስለነበረ ይህንኑ ትውፊት በማስቀጠል ወንድ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት በተወለደች በ80 ቀኗ እንደሚጠመቁ ሊቀ ሊቃውንት አብራርተዋል። በመጽሐፈ ኩፋሌ ምዕራፍ አራት እንደተጠቀሰው የሄዋን እጥፍ የኾነበት ምክንያት በሁለተኛው ሱባኤ ስለተፈጠረች ነውም ብለዋል።
የ40 እና 80 ድምር 120 ነው። መነሻቸው አዳም እና ሔዋን የኾኑት የክርስቶስ 120 (36ቱ ቅዱሳት፣ 72ቱ አርድእት እና 12ቱ ሐዋርያት) ቤተሰቦች መኾናችንን ለማዘከር በ40 እና በ80 ቀናችን የመጠመቃችን ሌላኛው ትውፊት መኾኑን ሊቀ ሊቃውንት ይተነትኑታል።
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት እና አሥራ ዘጠኝ ያለው ቃል የጥምቀትን ለምን እና እንዴትነት እንደሚገልጽ ጠቁመዋል። ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ ”እግዚአብሔር በመውረዱ፣ በመወለዱ እና በጥምቀቱ ምህረት፣ ይቅርታ እና ፍቅርን መስርቶልናል፤ የሰው ልጅ መለኮታዊ ባህሪን ተካፋይ ሊኾን የሚችለውም እነዚህን ነገሮች ሲያደርግ ነው፤ በክርስቶስ የሚያምን ማንኛውም ሰው ለሃይማኖቱ የሚገዛ እና ልብ የሚል ከኾነ እነዚህ ነገሮች ከእግዚአብሔር ከፈጣሪ የተሰጡን ናቸው” ብለዋል። ”ለሰዎች ይህንን በማድረጋችንም ፈጣሪያችንን እንመስለዋለን” ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ይህ ትልቅ ማዕረግ መኾኑን ገልጸዋል።
”ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው እንደሚልም ጠቅሰዋል። ልብ ብንል ፍቅርን ገንዘብ ብናደርግ ባለጸጎች እንኾናለን፤ በምድር ላይ በእረፍት እና በጸጥታ መኖር እንችላለን ሲሉም መክረዋል።
ቁጣ፣ ቅናት እና ጥላቻ በመጀመሪያ እረፍት የሚነሱን ራሳችን ነውም ብለዋል። ”ቁጡ ሰው በመኝታውም ላይ ሁከት ይበዛበታል ይጸናበታል እንጂ ሰላም እና ደስታ አይኖረውም” ያሉት ሊቁ ሰው ለራሱ በፍቅር ሲኖር የእግዚአብሔር ሰላምም በውስጡ እንደሚያድር ገልጸዋል።
ክርስቶስም የወረደው ለሰላም፣ ለይቅርታ እና ለፍቅር ነው፤ በክፋት መኖር የክርስቶስን ዓላማ ከንቱ ማድረግ ነው ብለዋል። ክርስቶስ ለምን ወረደ? ለምን ተወለደ? ብለን ማሰብ አለብን ነው ያሉት።
የመውረዱ፣ የመወለዱ እና የመጠመቁ ዓላማ ሰውን ማትረፍ ነው ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ እግዚአብሔር አክብሮ ያን ያክል ውለታ የሠራልን ሰዎች እርስ በርሳችን በይቅርታ በመዋደድ እና በሰላም መኖር እንደሚገባ መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!