
ባሕር ዳር፡ ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ የጥምቀት በዓል የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከብሯል።
ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ በተጨማሪ የጥምቀት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ መከበሩ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸው የበዓሉ ታዳሚ የእምነቱ ተከታዮች ገልጸዋል።
ላለፉት ዓመታት በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ጥምቀትን አለማክበራቸው ቁጭትን ፈጥሮባቸውን እንደነበር ያነሱት የበዓሉ ተሳታፊዎች ከነጻነት ማግስት በተከዜ ወንዝ ጥምቀትን በማክበራቸው ደስተኛ መኾናቸውን አንስተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ሀዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከባርነት ወደ ነጻነት ከሞት ወደ ሕይወት ለማሻገር በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ሰውነቱ እረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል ብለዋል።
የጥምቀት በዓል የምስጢራት ሁሉ መገለጫ ነው ያሉት መጋቢ ሀዲስ መምህር ዜናዊ ጥምቀት የስላሴ አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት እለት መኾኑንም አንስተዋል።
ጥምቀት የሰላምና የፍቅር መገለጫ በመሆኑ የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በስርዓተ ጥምቀቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከ27 ዓመት በኃላ በተከዜ ወንዝ የጥምቀት በዓልን ዳግም ለማክበር በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል ።
ጥምቀት የሰላም ተምሳሌት በመኾኑ ወጣቶች ሀገርን ከሚያፈርስ ድርጊት ተቆጥበው የሰላምን አስፈላጊነት በመረዳት በውይይትና በንግግር ልታምኑ ይገባል ብለዋል።
የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቶች ታጅቦ በሰቲት ሁመራ በድምቀት ተከብሮ ውሏል ።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!