
ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወልዶ በኢየሩሳሌም አደገ፡፡ በሰላሳ ሶስት ዓመቱም በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስ በቤተልሄም የተወለደበትን ዕለት በማስታወስ በረከት ለማግኘት ክርስቲያን ምዕመናን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉትን አድካሚ ጉዞ ለማስቀረት ላሊበላ ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን በላሊበላ እንደገነባ ሁሉ አፄ ፋሲለደስም ክርስቶስ የተጠመቀበትን የዮርዳኖስ አምሳል በጎንደር አቆመ፡፡
አፄ ፋሲለደስ የቀሃ ወንዝን በመጥለፍ ወደ አስገነባው የመጠመቂያ ገንዳ በማስገባት ከ200 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና በነበረችው ጎንደር ጥምቀት በየቦታው ተበታትኖ ሳይሆን ታቦታት በአንድ ላይ ተደብረው መከበር እንደሚገባቸው አዋጅ አስነገሩ፡፡
በጎንደር ከተማ የሚገኙት 44ቱ ታቦታት ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ገንዳው እስከተገነባበት ጊዜ ድረስ ጥምቀትን በቀሃ ወንዝ ዳርቻ በጋራ ሲያከብሩ ቆይተዋል፡፡
አጼ ፋሲለደስ በጎንደር ዘመንን እየሻረ የአዲስ ዘመን ትንሣኤን የሚያበስር ኪነ ህንፃ አስገነባ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በላሊበላ ሲከበር፤ ጥምቀቱ ደግሞ በፋሲለደስ የመጠመቂያ ገንዳ ዙሪያ በጎንደር እንዲከበር የድርሻቸውን ተወጡ ፡፡
ሁለቱም ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ ፈጠሩ፡፡ራስን መቻልን አስተማሩ፡፡ የጎንደር ፋሲለደስ ቤተመንግሥትም ሆነ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በዓለም የቅርስ መዝገብ ከሰፈሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓል የሆነው የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ ተመዝግቧል።
“የጥምቀት በዓል የመተሳሰብና የፍቅር የመገለጥ በዓል ነው” ጥምቀት ሞትን ድል የመንሳት ምልክት ከሞት ወደ ህይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገር ምልክት ነው! ጥምቀት ከወደቀው አሮጌው ሰው ማንነት ወደ አሸናፊ ወደ ሆነው አዲሱ ሰው ማንነት የመለወጥ ምልክት ነው።
በመሆኑም ከክርስቶስ ጋር አብረን በመጠመቃችን ሞቱን እንዲሁም ትንሣዔውን እንመስለዋለን በመሆኑም በዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በማየ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ መጠመቅን ስናብ እና ስናከብር የከተማችን የክልላችን እንዲሁም የሀገራችን ሕዝቦች መለያየትን በአንድነት ጥልን በፍቅር፣ ጨለማን በብርሃን፣ ድህነትን በብልፅግና ድል መንሳት ይገባናል።
ሺህ ዘመናት አሻግሮ ከዚህ ያደረሰን የአብሮ መኖር እሴታችንን፤ የመተሳሰብና የመተጋገዝ የቤተሰብ መንፈስ የሚታይበት ወጋችንን፤ የአባት የቅደመ አያት ልማዳችንን አፍርሰው፤ እንደ ውሻ አናክሰው ሊያጫርሱን የሚመኙም አሉ።
እኛ ግን በጋራ ታሪክና በወል ባህል ደም ተዛምደናል፡፡ ከደም የወፈረ የአንድነት ውኃ ጠጥተን፤ በቃል ኪዳን እምነት ተጋምደን፤
‹‹እኛ የኢትዮጵያ ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ የህብረት ገመድ ፈትለን፤ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የወግ፣ የትውፊት፣ የታሪክ፣ የዕድለ-ፈንታ ፈርጅ ተሳስረን፤ በሺ ዓመት ያልዛለ የአብሮነት መንፈስ ፈጥረን፤ በአንድነት ከፍቅር ህብስት ተካፍለን፤ በፈጣሪ ቸርነት ዕልፍ አመት ተሻገርን ይኸው ከዚህ ደርሰናል፡፡
የተከበራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በጥምቀት በዓል ከመላው የሀገራችን ክፍሎች እና የዓለም ሀገራት ጥምቀትን ለመታደም እንግዶች በከተማችን ጎንደር ክትመዋል። ስለሆነም በተለመደው የጎንደሬነት መገለጫችን “በመሰብ እንጀራ ፍየል በጉ ታርዶ ፤ ደስ ይለኛል ጎንደር ያውቃል መስተንግዶ” በሚል የሚታወቀው እንዲሁም እንብላ እንጠጣ አፈር ስሆን በሞቴ እያልን እያስተናገድን ለልጅ ልጆቻችን የሚነገር ታሪክ አብረን እንድንፅፍ ጥሪየን እያቀረብኩ በዓሉ የሰላም የፍቅር የደስታ የመተሳሰብ እንዲሆንልን ጥሪየን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም ይህ በዓል እንዲህ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አባታዊ ምክራችሁን ለሰጣችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ዲያቆናት ምስጋናየን በኔና በጎንደር ከተማ ሕዝብ ስም ላቀርብ እወዳለሁ በድጋሚ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንልን፡፡