ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

30

ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልእክታቸውም “ውድ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለጥምቀት በዓል በደኅና አደረሳችሁ” ብለዋል፡፡

በሀገራችን በአደባባይ ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የሆነው ጥምቀት በድምቀት እና በጽኑ መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ ልንከባከበው የሚገባ የዓለም ቅርስ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የጋራ ዓላማን ካወቁ፣ ካመኑ ከሚከፋፍላቸው በላይ የሚያስተሳሥራቸው እንደሚበልጥ በተደጋጋሚ አሳይተዋል፤ እያሳዩም ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ጥምቀትን ኢትዮጵያውያን እና ከዓለም ዙሪያ ከሚመጡ በርካታ ጎብኝዎች ጋር እንደተለመደው እናክብረው፤ ቅርስነቱን የሚያቆየው የበዓሉ በአግባቡ መከበር ነውና ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“ፈጣሪ ከሁላችን በላይ የኾነችውን ሀገራችንን አብዝቶ ይባርክልን፤ ሠላምን ያስፍንልን” ሲሉ መልእክት ማስተላለፋቸውን ከፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥምቀት ለሰው ልጅ ድኀነት የተሰጠ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
Next articleየጥምቀት በዓል በኮምቦልቻ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።