“ጥምቀት ለሰው ልጅ ድኀነት የተሰጠ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

66

አዲስ አበባ: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት የጥምቀት በዓል ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት እግዚአብሔር ጥምቀትን ሲያመጣ ለድኅነት እና ለተሻለ መዳን መኾኑ እሙን ነው ብለዋል። ለፍዳ እና ሀጢአት የተፈጠረውን የሰው ልጅ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳነው፤ ያን ደግሞ በጥምቀት በኩል አምጥቶታል ሲሉ ገልጸዋል።

በዛሬው እለት በዮርዳኖስ ወንዝ የተገለጠው ረድኤት እና የጥምቀት ምሥጢር ለሰው ልጅ መዳንም እምነት እና ጥምቀት ነው፤ እኛም እምነትን እና ቃልኪዳን ጠብቀን መኖር ግዴታ ነው ብለዋል።

ይህንን በዓል በስሙ እናከብረዋልን እንጂ በዓሉ የእኛ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም ምክንያቱም ጥቅሙ ለእኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል። እሱም የእውነቱ አምላክ የመጣው ሥራው ሁሉ ትምህርት በመኾኑ እኛ ትምህርቱን ወስደን መተግበር አለብን ብለዋል።

ስለዚህም እኛ ለሰው ልጅ ሁሉ የምናስተላልፈው ምክር ንስሀ ግቡ ነው። ሰው ንስሀ ከገባ መገዳደል፣ መስረቅ እና ሰላም ማጣት ይቀረፋል፤ ሰላም ይመጣል፤ መረጋገት እና ነፃነት ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

ዛሬ እኛ ይህንን በዓል ስናከብር በርካቶች ተርበዋል። ሌላው በርሀብ እየተቀጣ እኛ ዝም ካልን ክርስቲያናዊነት የት ላይ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። በመኾኑም በርሀብ ለተጎዱት ሁሉ በመላው ዓለም የምትገኙ እጃችሁን እንድትዘረጉ እንጠይቃለን ብለዋል።

የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለድኅነት እና ምኅርት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ይህንን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ቤተክርስቲያኒቱ ለረዥም ጊዜ ጠብቃ ኖራለች፤ ጥምቀት በዩኔስኮ ሊመዘገብ የቻለው ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቱ ከመንፈሳዊ ጋር ተዳምሮ በሰጠው ትርጉም የተገኘ ነው ብለዋል። ይህ ሀብት የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ለዚህም ነው ልዩ እና ሀገር በቀል በዓል ነው የምንለው ሲሉ ገልፀውታል። በዓሉ እንዳይበረዝ እና እንዳይደበዝዝ ሊጠበቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ሒሩት ካሳው ባስተላለፉት መልእክት ይህንን ጥምቀት በርካታ ዜጎች ከሀገር ተሻግረው ለማየት ይመጣሉ። በአግባቡ ጠብቀን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ሲሉ ገልጸዋል። እነዚህ በዓላት የሰላም በዓላት በመኾናቸው ፍቅር እና ሰላም እየሰበኩ መከበር ይገባቸዋል ብለዋል።

ዘጋቢ: አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያዊቷ ዳግማዊ ዮርዳኖስ፡ ኢራምቡቲ!
Next articleፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።