
ኢራቡቲ: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዳም ከ5 ሺህ 500 ዓመታት ፍዳ በኋላ ዳግም ልጅነትን ያገኝ ዘንድ ይች ቀን ትርጉም ነበራት፡፡ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሲያልፍ ፍሊጶስን ስለጥምቀት እንደጠየቀ ሁሉ ኢትዮጵያም ስለጥምቀት ጓዳ ጎድጓደዋን፤ ተራራ ሸንተረሯን ገና ከጥንት ጀምራ ፈትሻለች፡፡
ዳግማዊቷ ዮርዳኖስ ኢራምቡቲ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የጥምቀት ፍተሻ ውጤት ናት የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ በዮርዳኖስ ያለ ነገር ግን በኢራምቡቲ የሌለ ምን ተምሳሌት አለ፡፡
ኢራምቡቲ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ሸንኮራ ወረዳ የምትገኝ አንድ ቀበሌ ናት፡፡ በኢራምቡቲ የሚገኘው የሸንኮራ ወንዝ በየዓመቱ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል 44 ታቦታት በአንድ ተሰባስበው ይከትሙበታል፡፡
ከ18 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው የሚመጡት ታቦታት እና ምዕመናን ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በኢራምቡቲ ጥምቀትን ያከብራሉ፡፡
ጥምቀት በኢራምቡቲ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአጼ ዳዊት ዘመነ ንግሥና ጀምሮ ይከበር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ከ620 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው ጥምቀት በኢራምቡቲ የተለየ ድባብ እና ለዛ እንዳለው ይነገራል፡፡
በሰሜን ሽዋ ሀገረ ስብከት የሸንኮራ ወረዳ ቤተ ክህነት ኀላፊ ሊቀ ህሩያን ሞገስ ተፈራ ጥምቀት በኢራምቡቲ ዘመናትን ያስቆጠረ የተለየ ገጽታ እና ውበት ያለው በዓል ነው ይላሉ፡፡
በየአድባራቱ ያሉ ታቦታት በከተራ በዓል ወርደው በነጋታው እንዳመጣጣቸው በሆታ እና በእልልታ ታጅበው፤ መዘመራን እየዘመሩ ካህናት እያሸበሸቡ ይመለሳሉ፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ግን እስከ ቃና ዘ ገሊላ ድረስ በኢራምቡቲ ይቆያል ብለውናል፡፡
ኢራምቡቲ በተለይም ከአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ ንግሥና ጀምሮ በጥምቀት በዓል አከባበር ይበልጥ እየታወቀች መምጣቷን የሚናገሩት ሊቀ ህሩያን ሞገስ ከሀገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ሥፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን በርካታ ናቸው ብለውናል፡፡
ኢራምቡቲ ዳግማዊት ዮርዳኖስ ናት ሲባል መነሻው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ሊቀ ህሩያን ሞገስ ተፈራ ሲመልሱ ወንዙ ከላይ ከመነሻው አንድ ኾኖ መሃል ላይ ለሁለት ተከፍሎ ዝቅ ብሎ መገናኘቱ አንዱ አምሣለ ዮርዳኖስ ያሰኘዋል ብለዋል፡፡ ተፈጥሯዊ ወንዝ መኾኑ እና ውኃው ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ መፍሰሱ ዳግማዊ ያሰኘዋል ነው ያሉት፡፡ ለ44ቱ ታቦታት መጸበያ ቦታ መኖሩንም ነግረውናል፡፡
ኢራምቡቲ መሠረተ ልማት ከተሟላለት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሚጠቅም መልኩ ሁነኛ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ መኾን የሚችል መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ጥምቀት በኢራምቡቲ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በዓል ቢኾንም ማሕበራዊ መስተጋብሩም የጎላ በመኾኑ ፋይዳው በርካታ ነው ብለዋል፡፡ በጥምቀት የተራራቀው የሚገናኝበት፣ የትዳር አጋር የሚመረጥበት እና ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው የሚመለሱበት በዓል ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!