የጥምቀት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በልዩ ልዩ ክዋኔዎች እየተከበረ ይገኛል፡፡

40

ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በድምቀት በመከበር ላይ ነው። ለአብነትም ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ አውስትራሊያ፣ ሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ግሪክ፣ እና ዮርዳኖስ ጥምቀትን በማክበር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው፡፡

ጥምቀት በሩሲያ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጭምር በተገኙበት በቤተ-ክርስቲያናት በዝማሬ እና በአደባባይ ደግሞ በልዩልዩ ሃይማኖታዊ መዝሙሮች እንዲሁም ትርኢቶች ደምቆ ተከብሯል፡፡
አብዛኛው የዩክሬን ሕዝብ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ዩክሬናዊያንም የጥምቀት በዓልን ልክ አንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥር 11 ቀን ይከብሩታል፡፡

በጥምቀት ዕለት የእምነቱ ተከታዮች ወንዝ ውስጥ ይጠመቃሉ፤ የወንዝ ውኃ ነፍስን ያነጻል በሚል በውኃው እየተረጫጩ ያከብሩታል፡፡ አባቶችም ምእመኑን ወንዝ እና ሐይቅ ዳርቻ ላይ ኾነው ያጠምቃሉ፡፡

በግሪክ ደግሞ ቀደምት ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት ዋነኛው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በጥምቀት ዕለት ማለዳ ላይ አብያተ- ክርስቲያናት ደወል ያሰማሉ፡፡ ፓትርያርኩ በተገኙበትም ቅዳሴ ይደረጋል፡፡ በየአካባቢው ምእምኑ የጥምቀት በዓልን በወንዝ ዳርቻ ተሠባሥቦ ሃይማኖታዊ ዜማ እያሰሙ ቡራኬ ይቀበላሉ፡፡

በሀገረ አውስትራሊያ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ክዋኔዎች ይከበራል፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ሠብሠብ ብለው በማለዳ በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ ወንዝ ይወርዳሉ፡፡ ከየቅጣጫው የተሠባሠበው ምዕመንም ልዩ ልዩ ዜማዎችን በማሰማት ያደምቁታል፡፡

የእምነት አባቶችም በአበባ የተለበጠውን መስቀል ወደ ባሕሩ ይወረውሩታል፤ ምእመኑም መስቀሉን ፍለጋ ወደ ወንዙ እየተወረወሩ ይገባሉ፤ የሰመጠውን መስቀልም ፈልገው በማግኘት ይባረኩበታል፡፡ በመጨረሻም በልዩ ልዩ ትርኢት ቀኑ ተከብሮ ይውላል፡፡

በሩማኒያ የጥምቀት በዓል የሚከበረው የሃይማኖት ዓባቶች በወንዝ ላይ በጀልባ እየቀዘፉ መስቀሉን በመደበቅ ነው፡፡ ምእመኑም ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን በመኾን መስቀሉን ፈልገው በማግኘት በካህናት ይሳለሙታል፡፡ ቀኑን ሙሉም በጎዳና ላይ ትርኢቶች በዓሉ በድምቀት ሲከበር ይውላል፡፡

በሩማኒያ በጥምቀት ዕለት ፈረሶች እና ሰረገላዎች በጌጣጌጥ አሸብርቀው ጥምቀቱን ያደምቁታል፡፡ የሃይማኖት አባቶችም በምእመኑ ታጀበው፣ በልዩልዩ ዜማዎች ተውበው መንገድ ዳር ላይ ኾነው አላፊ አግዳሚውን በጸበል ይረጫሉ፤ ያጠምቃሉ፡፡

በቡልጋሪያ የጥምቀት በዓል የሚከበረው ምእመኑ በነጭ አልባሳት ደምቀው፣ ከበሮ እየመቱ እና አርሞኒካ እየነፉ ከወንዙ ጸበል በመረጨት ነው፡፡

ጥምቀት በላቲን አሜሪካ የሰባ ሰገልን ቀን ተከትሎ ይከበራል፡፡ በአሜሪካም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከብሮ ይወላል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል በኮምቦልቻ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያዊቷ ዳግማዊ ዮርዳኖስ፡ ኢራምቡቲ!