
ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በኮምቦልቻ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጥምቀት በዓል በአደባባይ ከሚከበሩና በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ተብለው ከተመዘገቡ ቅርሶች አንዱ በመኾኑ ሀገራችንን በዓለም ደረጃ የሚያስዋውቅ በዓል በመኾኑ ቤተ ክርስቲያኗ በዓሉን በድምቀት ስታከብረው ከተማ አሥተዳደሩ ትልቅ ክብር አለው ብለዋል።
ሀገራችን በተፈጥሮ ፀጋ ከታደሉ ሀገሮች መካከል አንዷ ብትኾንም ዕርስ በርዕሳችን በምንፈጥረው ግጭት ከዚህ ዘርፍ በሚገባን ልክ ተጠቃሚ አልኾንም ብለዋል ከንቲባው በመልዕክታቸው።
ሀገራችን የብዝኀ ሃይማኖትና ብሔር መገኛ በመኾኗ ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር ተከባብረንና ተቻችለን ጉዳዮችን በሰከነና በተረጋጋ መልኩ በማየት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት አለብን ብለዋል ከንቲባው።
ከተማ አሥተዳደሩ የሃይማኖት ተቋማቶች የሰብዕና መገንቢያ መኾናቸውን ስለሚያምን ያሉ ጥያቄዎችን ደረጃ በጀረጃ ይፈታል በማለት አቶ መሀመድ አሚን አብራርተዋል።
በበዓሉ ላይ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ጨምሮ ሌሎች የመምሪያ የሥራ ኀላፊዎች መገኘታቸውን ከኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!