
እንጅባራ: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን አብነት በማድረግ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በልዩ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የሚከበር በዓል ነው።
በእንጅባራ ከተማ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም በኢትዮጵያዊ የባሕል አልባሳት አምረው እና ደምቀው በዓሉን በልዩ መንፈሳዊ ሥርዓት አክብረዋል።
በበዓሉ ስብከተ ወንጌል የሰጡት በመንበረ ፀሐይ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሐዲሳትና የብሉያት መምህር መጋቤ ብሉይ ወሀዲስ ሰናይ ክንዴ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪ ኾኖ ሳለ በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ ዝቅ ብሎ በመጠመቅ ለሰው ልጆች ትህትናን ያስተማረበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።
መጋቤ ብሉይ ወሀዲስ ሰናይ የእምነቱ ተከታዮች ትህትናን፣ ፍቅር እና ሰላምን የየዕለት የህይወት መመሪያቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራት የተደራጁ ወጣቶችም ታቦታት የሚያልፉባቸውን ጎዳናዎች እና ባሕረ ጥምቀቱን በማጽዳት፣ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ በማስዋብ እና በማስተባበር በዓሉ በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ሥርዓተ ቅዳሴው ተጠናቅቆ፣ በአባቶች ቡራኬ እና ሥርዓተ-ጥምቀቱ ተፈጽሞ ታቦታት ወደየ መንበረ ክብራቸው እየተሸኙ ነው።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!