
ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ትሕትናው የተገለጠበት፤ ባሕር የሸሸችበት፤ የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበት፤ ጠላት ድል የተመታበት፤ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ የረበበት፤ ፍጡር ፈጣሪውን ያጠመቀበት፤ ፈጣሪም ስለ ትሕትና በፍጡሩ እጅ የተጠመቀበት፤ በባርነት የኖረው የአዳም ዘር ነጻ የወጣበት የረቀቀ ምስጢር፡፡ የከበረ ጥምቀት፡፡
በጥምቀቱ ዘላለማዊ ልጅነትን ሰጣቸው፤ በጥምቀቱ ነጻነትን አወጀላቸው፤ በጥምቀቱ ከበደል እና ከሐጥያት አነጻቸው፤ በጥምቀቱ ግርማን አላበሳቸው፤ በረከትን እና ረድኤትን አደላቸው፡፡ በጥምቀቱ ወደ ክብራቸው መለሳቸው፤ ከጠላቶቻቸው አልቆ አስቀመጣቸው፤ የተለያዩትን አንድ አደረጋቸው፤ ያዘኑትን አረጋጋቸው፤ የታሰሩትን አስፈታቸው፡፡
ክርስቲያኖች የጥምቀቱን ነገር ያስቡታል፤ የጥምቀቱን ነገር እጹብ እያሉ ያደንቁታል፤ በጥምቀቱ ያምኑበታል፤ ይመኩበታል፤ በጥምቀቱ የአምላካቸውን ስም እያነሱ ያወደሱታል፤ ያመሠግኑታል፤ እንዲህ ያለ ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው? እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው? እንዲህ ያለ ምስጢር እንደምን ያለ ሚስጥር ነው? እያሉ ምሥጋና ያቀርባሉ፤ አንደበታቸውን በውዳሴ ይመላሉ፡፡
አንዳንድ ወንዞች አሉ ምንጫቸው ከገነት የሚመነጭላቸው፤ አንዳንድ ወንዞች አሉ የረቀቀ ምስጢር የሚመሰጠርባቸው፤ አንዳንድ ወንዞች አሉ ሃይማኖት የሚገለጥባቸው፤ ትሕትና የሚታይባቸው፤ ቅዱስ መጽሐፍ ስማቸውን የመዘገባቸው፤ አራቱ ታላላቅ አፍላጋት በአምላክ ጥበብ ገነትን አጠጥተዋል፤ ባሕረ ኤርትራ በአምላክ ጥበብ ተከፍሎ እስራኤላውያንን አሻግሯል፤ ዮርዳኖስም ታቦተ ጽዮንን ባየ ጊዜ ከሁለት ተከፍሏል፤ መንገዱን ለቆ ታቦተ ጽዮንን አሻግሯል፤ ስለ አምላኩ ክብር ሸሽቷል፡፡
አስቀድሞ ገና ትንቢት ተተንብዮለታል፤ አምላክ እንደሚጠመቅበት፤ ተጠምቆም በዚያ ውስጥ የተቀበረውን የእዳ ደብዳቤ እንደሚቀደድበት ባሕረ ዮርዳኖስ፡፡ አንቺ ዮርዳኖስ ኾይ መታደልሽ? ፈጣሪሽን አጥምቀሻል፤ በመንፈስ ቅዱስ ተመልተሻል፤ በቅዱሳን እግሮቹ ተረግጠሻልና፤ መጥምቁ ዮሐንስ ኾይ መታደልህ? ፈጣሪህን አጥምቀሃልና፤ የአምላክህን ትሕትና ተመልከተሃልና፤ ምጥምቀ መለኮት እየተባልክ ተጠርተሃልና፡፡
አጥማቂው በተጠማቂ እጅ መጠመቅ እንደምን ያለ ነገር ነው? አገልጋዮቹ እባክህን አጥምቀን ብለው ሊለምኑት ሲገባ እርሱ ግን አገልጋዩን አጥምቀኝ አለው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የጌታ ጥምቀት በዓል ያለው ክብር አምላክ እርሱ የመረጠው፣ እርሱ ራሱ የተጠመቀው ነው፤ የእርሱ ጥምቀትም በእርሱ አርዓያ ለተፈጠሩ ፍጥረታት ሁሉ መድኃኒት፤ ልደት ኾኖ የተሰጠ ነው ይላሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ለሰው ልጆች ልጅነትን ማግኛ ነው፤ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ልጅነትን ያገኙበት ነውና፡፡
ሊቁ እንደሚሉት በሕገ ኦሪት ዘመንም ጥምቀት ነበር፤ ያም ጥምቀት የንስሃ ጥምቀት ነበር፤ በብሉይ ኪዳን በኦሪት ሕግ የተከለከለውን የሚነኩ ሁሉ በጥምቀት ይነጹ ነበር፡፡ የተከለከለውን የነኩት የሚነጹት በሚረጭ ውኃ ነው፤ ጸሎትን አድርገው ሲረጯቸው በስጋ ይነጹ ነበር፡፡ ከአጥማቂዎችም አንደኛው ዮሐንስ ነበር፡፡ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ኾኖ የሚመጡትን የንስሃ ጥምቀት ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ንስሃ እየሰጠ እያጠመቀ ሳለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
የኔታ ሲናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስም በፈለገ ዮርዳኖስ እያጠመቀ የነበረውን ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው፡፡ ዮሐንስም እኔ ከአንተ መጠመቅ ይገባኛል እንጂ እንዴት አንተን አጠምቃለሁ አለው፡፡ ደቀመዝሙር በመምህሩ እጅ ይጠመቃል እንጂ መምህር በደቀመዝሙሩ፤ ፍጡር በፈጣሪው እንጂ ፈጣሪ እንዴት በፍጡሩ እጅ ይጠመቃል አለ፡፡ ጌታም አንድ ጊዜ ብቻ ታጠመቀኛለህ አለው፤ አንድ ጊዜ ብቻ ታጠምቀኛለህ ማለቱም ጥምቀት አንዲት ብቻ መኾኗን ሲያመላክት ነው ይላሉ፡፡
ጥምቀቱ ለእኔ እና ለአንተ ትልቅ ደስታ ነው፤ አንተ እኔን አጥምቀህ መጥምቀ መለኮት እየተባልክ ልዕልናህ፣ ከፍታህ ክብርህ ሲነገርልህ ይኖራል፤ እኔ ደግሞ አምላክ ስኾን ከሰማየ ሰማያት ወርጄ፣ ከድንግል ማርያም ተወልጄ በዮርዳኖስ ስጠመቅ ትሕትናዬ ይነገራል፤ ፈጣሪ በፍጡር እጅ ተጠመቀ ተብሎ የእኔ ትሕትና የአንተ ክብር እና ልዕልና ይነገርበታል እና አጥምቀኝ አለው ይላሉ አበው፡፡ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውም አለው፡፡ ዮሐንስም እሽ ብሎ ጌታውን አጠመቀው፤ ጌታም ተጠመቀ፡፡
ያን ጊዜ ባሕር ሸሸች፤ ደነገጠች፡፡ ውኃዎች አይተው ሸሹ፤ ባሕር የሸሼሽ ምን ኾነሽ ነው? አንተ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለስክ ለምንድን ነው? ተብሎ አስቀድሞ ገና በትንቢት የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ዮርዳኖስ ከጌታ መጠመቅ አስቀድሞ ምስጢራት ሲካሄዱበት የኖረ ነው፡፡ መስፍኑ ኢያሱ መሪነትን ከሙሴ ተቀብሎ እስራኤላውያንን ወደ ምድረ እርስት እየመራ ባለ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፡፡ በዚያም ጊዜ አምላክ ዮርዳኖስ እንደሚቆምላቸው ለኢያሱ ነገረው፡፡ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው በወንዙ ዳር እንዲቆሙ፤ ሕዝቡ ከታቦቱ ሁለት ሺህ ክንድ እንዲርቅ ነገረው፡፡ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ዮርዳኖስ በደረሱ ጊዜ ዮርዳኖስ ከሁለት ተከፈለ፡፡ በዚያም ጊዜ ተሻገሩ፡፡ ታቦቱም የጌታ ምሳሌ ነው፡፡
ለጥምቀት ጌታ ከገሊላ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ እንደ ወረደ ሁሉ ጥምቀት በደረሰ ጊዜ ዛሬም ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ይወርዳሉ ይላሉ ሊቁ፡፡ ታቦታቱም በጥምቀተ ባሕር አርፈው ማሕሌት ይቆማል፤ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ባሕሩ ይባረክ ዘንድ ጸሎት ተደርሶ፤ ባሕሩ ይባረካል፡፡ ሕዝብም ይጠመቃል፡፡ ጸሎቱ በተፈጸመም ጊዜ ታቦታቱ በታላቅ ክብር ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ፡፡
ሊቁ ባሕረ ዮርዳኖስ ከግዮን ጋር ይመሳሰላል ይላሉ፡፡ ግዮን በጣና ላይ እንደሚሄድ ሁሉ ዮርዳኖስም በባሕረ ገሊላ ላይ ይሄዳል፡፡ ዮርዳኖስ ዮር እና ዳኖስ ተብሎ በሁለት ተከፍሎ ይመጣል፡፡ ባሕረ ገሊላ ላይም አንድ ኾኖ ይፈስሳል፡፡ ጌታም የተጠመቀው አንድ ከኾነው ከዮርዳኖስ ነው፡፡ ይህም በጥምቀቱ ሕዝብ እና አሕዛብን አንድ ስለማድረጉ ምስጢር ነው ይላሉ ሊቁ፡፡ በጥምቀቱ አንድነቱን ሰጥቷል፤ ኢየሱስ ክርስቶ በጥምቀቱ እና በስቅለቱ የሰውን ልጅ ነጻነት አውጇል፤ ባርነትን ሰርዟል፡፡ የእርሱ መጠመቅ ለሰው ልጅ መዳን ለመስጠት የተጠቀመበት ነውና፡፡ ለሰው ልጅ እኩል የኾነ ድኅነት፣ እኩል የኾነ ነጻነት የሰጠ የማያዳላ አምላክም መኾኑን ያሳየበት ነው ይላሉ፡፡
ዲያቢሎስ አዳምና ሔዋንን ተገዢዎቹ እንደኾኑ በእብነ መበረድ ጽፎ በዮርዳኖስ አስቀምጦት ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሊያድን የእዳ ደብዳቤውን ሊቀድ በወደደ ጊዜ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ በዮርዳኖስም ሄዶ ዮሐንስን አጥምቀኝ ብሎ የቆመበት ዲያቢሎስ ደብዳቤውን ካስቀመጠበት ሥፍራ ላይ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጠፋላቸው፡፡ ሊቁ እንደሚሉት የጥምቀት በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የነጻነት በዓል ነው፡፡ የነጻነት በዓል ነውና ጥምቀት ልዩ ኾኖ ይከበራል፡፡
በጥምቀት ጠላት የተረታበት፣ እዳ የተሰረዘበት፣ የሰው ልጅ ነጻ የወጣበት ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ሀገረ እግዚአብሔር እየተባለች በምትጠራው በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያ አስቀድሞ ገና አምላክን ስታስብ የኖረች፣ የአምላክን ስም ስታመሠግን የኖረች ናት፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ሁለተኛ የተወለደ ወደ እግዚብሔር መንግሥት ይገባል፤ ሁለተኛ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም በሚለው ቃል መሠረት ያመኑ ያከብሩታል፡፡ ያስቡታል፡፡ ቃሉን ይፈጸሙታል፡፡ አስቀድሞ ገና እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ተብሎ የተነገረላት ሀገር ኢትዮጵያ ሕጉን ስትጠብቀው ኖራለች፡፡ እግዚአብሔርን በአንድነቱ እና በሦስትነቱ ታውቀዋለች ይላሉ ሊቁ፡፡
የክርስቶስን መወለድ እየጠበቀች የቆየች ሀገር ናት፡፡ በእግዚአብሔር አምልኮ የቆዬችም ሀገር ናት፡፡ ለልደቱም ለጌታ የእጅ መንሻ ያቀረበችም ሀገር ናት ነው የሚሉት፡፡ ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን በጃንደረባው አማካኝነት እንደኾነ ነው የሚናገሩት፡፡
“እነሆም የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ ከሹሞቹም የበለጠ በሀብቷም ሁሉ ላይ በጅሮንድ የነበረ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ ሲመለስም በሰረገላው ላይ ተቀምጦ የነብዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡
መንፈስ ቅዱስም ፊልጶስን ሂድ ይህንን ሰረገላ ተከተለው አለው፡፡ ፊልጶስም ፈጥኖ ደርሶ የነብዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማው፡፡ ፊልጶስም በእውኑ የምታነበውን ታውቃለህን? አለው፡፡ ጃንደረባውም ያስተማረኝ ሳይኖር በምን አውቀዋለሁ? አለው፡፡
ወደ ሰረገላውም ወጥቶ አብሮት ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፡፡ …. ፊልጶስም አስተማረው፡፡ በመንገድ ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፡፡ ጃንደረባውም እነሆ ውኃ መጠመቅን ምን ይከለክለኛል? አለው ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ይገባሃል አለው፡፡ ጃንደረባውም መልሶ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚብሔር ልጅ እንደኾነ እኔ አምናለሁ አለው፡፡ ሰረገላውንም እንዲያቆሙ አዘዘ፡፡ አቁመውም ፊልጶስ እና ጃንደረባው በአንድነት ወደ ውኃ ወረዱ፡፡ አጠመቀውም፡፡ ተብሎ እንደተጻፈ ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በጃንደረባው አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ዘመን በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ነው፡፡
ለማጥመቅ ካህናት ያስፈልጋሉና ጥምቀት መከበር የጀመረው ግን አባ ሰላም ከሳቴ ብርሃን አባ ፍርሚናጦስ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡
ካህናቱ እያጠመቁ፣ ጥምቀትን አከበሩ፡፡ ይህም በዓል ሕግና ሥርዓቱ እየተከበረ ለዘመናት ዘለቀ ነው የሚሉት፡፡ ነገሥታቱ ያከብሩታል፤ መሳፍንቱ እና መኳንንቱም የጌታን ጥምቀት ይመኩበታል፤ የጦር አበጋዞችም በጌታ ጥምቀት ወደ ጥምቀተ ባሕር እየወረዱ ይጠመቁበታል፤ ምዕመናኑም ታቦታትን አጅበው፣ በምሥጋና እና በእልልታ ጥምቀትን ያከብራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ይጠመቃሉ፡፡
እነሆ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የጌታቸውን እና የመድኃኒታቸውን ጥምቀት ያከብራሉ፡፡ ካህናቱ ታቦታትን ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ይሸከማሉ፡፡ ኀይልና ብርታቱን እንዲሰጣቸው እየተማጸኑ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይጓዛሉ፡፡ ምዕምናኑም አንደበታቸውን በምሥጋና ይመላሉ፤ ታቦታትን ይከበክባሉ፤ ወደ ጥምቀተ ባሕር እየወረዱ በመንፈስ ቅዱስ በተባረከው ባሕር ይጠመቃሉ፤ በጥምቀትም መዳንን ያገኛሉ፤ ልጅነትን ይቀበላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በጥምቀት ትዋባለች፤ ትቀደሳለች፡፡ ትደምቃለች፡፡ በጥምቀት ከዳር ዳር በምሥጋና ትመላለች፡፡ በውዳሴ ትከበባለች፡፡ እነሆ ጥምቀት ነውና አፍላጋት ተባርከዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰዋል፡፡ ክርስቲያኖቹም በዚያ ሥፍራ ተሰባስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!