
ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በመናገሻዋ ከተማ ጎንደር እየተከበረ ነው፡፡ ቀደም ባለው ዘመን ቅጽር እና ቅጽራቸው በገጠሙ አርባ አራት ታቦታት የምትታወቀው ጎንደር በዚህ ዘመን ከአርባ አራቱ የሚልቁ ታቦታት አሏት፡፡
የጥምቀት በዓል ታላቁ ንጉሥ አጼ ፋሲለደስ ባሠሩት ጥምቀተ ባህር ውስጥ እየተከበረ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሚስጥረ ጥምቀትን የመሠረተበት ቀን ነው ብለዋል፡፡
ጌታ ተጠምቆ ሲወጣ ሰማይ ስለተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ከጌታ ራስ ላይ ስለተቀመጠ፣ አብም በሰማይ የምወደው ልጄ እርሱ ነው ብሎ ስለተናገረ፣ አንድነት እና ሦስትነት የተገለጠበት ቀን ስለኾነ መገለጥ ተብሎ እንደሚጠራም አንስተዋል፡፡
የጌታ ጥምቀት ፍጹም ትሕትና የተያበት ነው፡፡ ትሕትናውም የታየው ከጽንሰቱ ጀምሮ ነው፤ እርሱ ስለ እናንተ ደሀ ኾነ እንደተባለ ትሑት ነው ብለዋል፡፡ የነቢያት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶ ተወለደ ነው ያሉት፡፡
ብፁዕነታቸው ሲናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ባይወለድ ኖሮ ትንቢት ሁሉ በቀረ ነበር፤ ነገር ግን የማያደርገውን የማይናገር፣ የተናገረውን የማያስቀር፣ ሀሰት የሌለበት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የሰጠው ተስፋ፣ በነብያት ያናገረው ትንቢት በቀረበ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ነው ያሉት፡፡
አምላክ የሠራውን ሥራ ሁሉ አስቀድሞ በነብያት የተነገረው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ትምህርት የሰጡት የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም አሥተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ክርስቶስ ሕግን ፈጸመ ብለዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን ሊፈጽም መጸነሱን፣ መወለዱን፣ ማደጉን፣ መጠመቁን፣ መሰቀሉን፣ መነሳቱን እና ማረጉን ተናግረዋል፡፡ ክርስቶስ ከሰው በተለየ ጽንሰት ዘር ሳይቀድመው፣ የእናቱን ማሕተመ ድንግልና ሳይለውጥ መጸነሱን እና መወለዱንም አንስተዋል፡፡
ከመጠመቁ በፊትም ኾነ ከተጠመቀ በኋላ በምድር ላይ ያደረጋቸው ሁሉ ሕግን የሚፈጽምባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ጥምቀት ሕግ ነው፣ ሥርዓት ብቻ አይደለም፡፡ የተጠመቀ ይድናል፣ ያልተጠመቀ አይድንም እንደተባለ ጥምቀት ሃይማኖታዊ ሕግ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን