
ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጥምቀት በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ሃይማኖታዊ እና የአደባባይ በዓል ቢኾንም በጎንደር ደግሞ ድባቡ ይለያል።
አንድም “የአፍሪካ ካሜሎት” እያሉ የሚጠሯት መናገሻዋ ጎንደር ለረጂም ዘመናት 44 ታቦታትን አቅፋ እና ሸክፋ የያዘች ምድር መኾኗ ነው።
ሌላው ደግሞ ዘመናትን በተሻገረው የጥምቀት በዓል ውስጥ ታቦታቱ በከተራ ቀን ወርደው ጥንታዊ በኾነው እና በታሪካዊው ቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ማደራቸው ጥምቀትን በጎንደር ልዩ ያደርገዋል።
ዛሬም እንደ ትናንቱ በከተራው ቀን ወደ ጥምቀተ ባሕሩ በአጀብ ካወረዷቸው ታቦታት ጋር ጧፋ እያበሩ በዚያው የሚያድሩ ብርቱ ምዕመናን አሁንም እልፍ ናቸው።
ቀሳውስቱ በቅዳሴ እና በውዳሴ፤ የጎንደር ሊቃውንትም በስብከት እና በጸሎት ማዕልቱን ሙሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እያደረሱ በዚያው ቁመው ያነጋሉ።
ጥንታዊ የፋሲለደስ መዋኛ በጥምቀት ሌሊት ከሰማይ ከዋክበት በሚስተካከል ጧፍ እና ሻማ፤ ከምድር አሽዋ በሚጠጋ ምዕመን ደምቆ እና ተውቦ ያድራል። ይኽች ሌሊት በጎንደር ሰማይ ስር በእውነትም የተለየች ናት።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያም የጥምቀትን ሌሊት በጎንደሩ የቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ተገኝቶ ድባቡን እየቃኘ ነው። የሌሊት እና የአነጋግ ድባቡን ለተከታዩቹ በፎቶ እንዲህ አስቃኝቷል፦
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!