
ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጥምቀት ከተራ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት በዓላት ውስጥ አንዱ የጥምቀት በዓል መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመካከላችን መከባበር መደጋገፍ እና ፍቅርን በማስቀደም የክርስቶስን አርዓያነት መከተል ይገባናል ብለዋል።
”ክርስቶስ ያስተማረን ትህትና ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ትህትና ተሸናፊነትን ኾነ ደካማነትን የሚያሳይ ሳይኾን ትዕግስትን፣ ማስተዋልን እና ይቅር ባይነትን የሚያሳይ እንደኾነ ገልጸዋል።
“ጥላቻን በፍቅር መለወጥ፣ በቀልን በይቅርታ ማሸነፍ፣ ግጭትን በእርቅ መዝጋት ተገቢ መኾኑን በጥምቀቱ የምናምን ሰዎች ባሕላችን እና እሴታችን ሊኾን ይገባል” ብለዋል።
ባለፉት ወራት በክልሉ እና በከተማዋ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ችግሮች ቢኖሩም አሁን ላይ የክልሉ እና የከተማዋ የሰላም ሁኔታ ተሻሽሏል ነው ያሉት።
ይህም የኾነው የሰላም ሁኔታው በአርቆ አሳቢነት እና በሰላም ወዳዱ ሕዝብ አስተዋይነት እንደኾነ ተናግረዋል። ሕዝቡ ላሳየው የሰላም ወዳድነት፣ ፍቅር እና ፍላጎት አመሥግነዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችም ከተማቸውን ከችግር እና ከጥፋት ለመጠበቅ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ክብር ሰጥተዋል።
የሃይማኖት አባቶች ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መተሳሰብ እና እርቀ ሰላምን በመስበክ አባታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም እንዲከናወን ለተጉ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ምሥጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!