
ሰቆጣ: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደበትን የትህትና ጉዞ ምክንያት በማድረግ ታቦታቱ በዮርዳኖስ አምሳል ወደተዘጋጀላቸው የጥምቀት ማደሪያ ይወርዳሉ።
በሰቆጣ ከተማም ይህንን አብነት በማድረግ ሦስቱ አድባራት ወደ ተዘጋጀላቸው የጥምቀት ማደሪያ እየወረዱ ይገኛሉ።
በከተራ በዓሉም የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ ሕዝበ ክርስትያኑን ባርከዋል።
በጥምቀት ከተራ በዓሉም የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ ዘማርያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና የሃይማኖቱ ተከታዮች በእልልታ እና በዝማሬ እያከበሩ ይገኛሉ።
በጎ አድራጊ ወጣቶችም መንገዱን በመጥረግ እና ምንጣፍ በማንጠፍ ታቦታቱን እያጀቡ ይገኛሉ።
የተደራጁ ወጣቶችና የጸጥታ አካላትም ከሕዝበ ክርስትያኑ ጋር በመኾን በሰላም የከተራ በዓሉ እንዲፈጸም ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!