
ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጥምቀት በጎንደር ታቦታቱ በእልልታና ጭብጨባ ከመንበራቸው ወደ ቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀት ባሕር እየወረዱ ነው።
ጥምቀትን በጎንደር ልዩ መልክ እንዲኖረው ካስቻሉ ምክንያቶች ውስጥ የቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ወይም ደግሞ ፋሲል መዋኛ አንዱ ነው። ባሕረ ጥምቀቱ በአጼ ፋሲል ነው የተገነባው።
ይህ ውብ ባሕረ ጥምቀት ከዋናው የአጼ ፋሲል ቤተ መንግሥት ግቢ በምዕራብ አቅጣጫ በ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ባሕረ ጥምቀቱ ጎንደርን ከሁለት ከፍሎ ከሚያልፈው ቀሃ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኝ ሰፊ ግቢ ነው፡፡
ግቢው በዙሪያው 6 የእንቁላል ቅርጽ ያላቸው ግንቦች አሉት። በአማካኝ 50 ሜትር ርዝመት እና 30 ሜትር ስፋት አለው። ባሕረ ጥምቀቱ እምነትን፣ ታሪክን እና ውበትን አጣምሮ ይዟል። በዙሪያው የሚገኙ ትልልቅ ሀገር በቀል ዛፎችም ለባሕረ ጥምቀቱ አጸድ ልዩ ውበት ሰጥተውታል።
ዞብል የተባለው ተወዳጁ የአጼ ፋሲል ፈረስ መቃብርም የሚገኘው በዚሁ ግቢ ነው፡፡ ባሕረ ጥምቀቱ ከቀናት በፊት የሚሞላ ሲኾን እጅግ በርካታ ሰዎችን በአንድ ላይ የሚያስተናግድ ነው።
የጎንደር ታቦታት በቀሳውስት ዝማሬ፣ በምእመናኑ እልልታ፣ በወጣቶች አጀብ እና ክብካቤ ወርደው በውቡ የቅዱስ ፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት አርፈዋል። ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሁሉ በዚሁ ሲከናወን ያድርና ነገ በጠዋቱ ደግሞ ሥርዓተ ጥምቀቱ ይካሄዳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!