
ደብረ ማርቆስ: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ለወራት ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር በመፍታት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥ ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወትን እንዲመራ ዓላማ ያደረገ ውይይት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
በክልሉ ለወራት ያጋጠመው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ነገሮችን በሰከነ መንገድ መገንዘብ እና በጋራ መቆም ያስፈልጋል ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ናቸው፡፡
ዶክተር ድረስ የጋራ የሰላም እሴቶችን በመጠቀም ግጭት እንዲቆም መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ የተፈጠረው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ መንግሥት በሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች ሰላም እንዲረጋገጥ በሃሳብ ማሸነፍ እና የሀገሪቱን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መሥራት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል። ነዋሪዎቹ መንግሥት የኑሮ ውድነትን እና ሥርዓት አልበኝነትን ለመከላከል እንዲሠራም ጠይቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል እዘዘው መኮንን የተፈጠረው ግጭት ክልሉን ለተጨማሪ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዳይዳርግ ማኅበረሰቡ ለሰላም ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በመድረኩ ካለፉት ችግሮች እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት በጦርነት ምክንያት ከገቡበት ቀውስ በመማር ከግጭት ለመውጣት ሁሉም ለመፍትሄው እንዲረባረብ ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡- ወንድወሰን ዋለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!