“ከተራ የትህትና አንዱ መገለጫ በዓል ነው” ሊቀ ጉባኤ መጋቢ ሳሙኤል እንየው

34

ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተ ክርስቲን ሥርዓት እና ትውፊት መሰረት ጥር 10 ቀን የከተራ በዓል ይከበራል፡፡ ስለ በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ዳራ በበዓሉ መደረግ ስላለበት ጉዳይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ዘርዘር ያለ ሃሳባቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

ከተራ ማለት ምን ማለት ነው ?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ ሊቀ ጉባኤ መጋቢ ሳሙኤል እንየው ከተራ ማለት የተከበበ ወንዝ አለያም የቆመ ወንዝ ማለት ነው ይላሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሲሄድ ሲወርድ የነበረው ወንዝ ባለበት እንደቆመ እና በገጠር አካባቢ የከተራ በዓል የሚከበረው ወንዝ ወይም ምንጭ ተገድቦ ካህናት ዙሪያውን ከበው ሥርዓተ ቅዳሴ ተቀድሶ እና ተባርኮ ስለኾነ ከተራ የሚል ስያሜ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

የከተራ በዓል የጥምቀት ዋዜማ ተብሎ ይጠራል፡፡ ታቦተ ሕጉ በምዕመናን ታጅቦ ወደ ወንዙ የሚወርድበት ቀን እና ሥርዓትም ነው፡፡ ሊቀ ጉባኤ ሳሙኤል የከተራ በዓልም ከቤተ ክርስቲያን ታቦታት ተይዘው ወደ ወንዝ የሚወረደው አንድም ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን ለማመልከት፤ ሁለትም ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን ለማስታወስ እና ለማሰብ ነው ብለዋል፡፡

በከተራ ዕለት የሚከወኑ ዋና ዋና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ምንምን ናቸው?
በየቤተክርስቲያኑ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ ካህናት ሊቃውንት ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ ቀጥሎም ቤተክርስቲያኑ ለከተራው እና ለጥምቀቱ ቦታ እንዳለው ርቀት ከ8፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው በካህናት ወረብና ሽብሸባ፣ በሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ፣ በምዕመናን እልልታ እና ሆታ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ቦታ ይወርዳሉ ብለዋል፡፡

ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ከከተራው ቦታ ተደርሶ ሊቃውንት እና የሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ አቅርበው፣ በዓሉን እና አከባበሩን አስመልክቶ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ እና ጸሎት ተደርጎ ታቦታቱ ወደ ድንኳናቸው እንደሚገቡ ሊቀ ጉባኤ አስረድተዋል፡፡ በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች በረከቱን ማግኘት ይችሉ ዘንድ ታቦታት የሚወርዱበትን የከተራ እና የጥምቀት ቦታ በየዓመቱ በየአቅጣጫዎቹ በመቀያየር እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

በከተራ ዕለት ምን ይደረጋል? ምንስ ይደረግ?
በከተራ በዓል እና በጥምቀት በዓል ጊዜ ሁሉም እኩል ነው፤ የበላይ የበታች አይታይበትም፡፡ ንጉስ ዳዊት ለታቦተ ጽዮን ልብሰ መንግሥቱን አውርዶ ታቦተ ጽዮንን በእልልታ አክብሯል፡፡ የዘመናችን ትውልድም በዓሉን ሥርዓተ ቤተክርስቲያኑን ጠብቆ መንገድ ማጽዳት፣ ሰላም ማስከበር፣ በሰረገላ ማጀብ፣ በጭብጨባ፣ በእልልታና በሆታ ታቦታቱን አጅቦ በዓሉን ማክበር ድሮም የነበረ ነው፤ ዛሬም ሊቀጥሉ የሚገባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ከሚገባው በላይ በመጠጣት፣ በቡድን መጋጨት፣ ለመበቃቀል መምጣት እና መሰል ባህርያት ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ፣ ከሃይማኖት እና ከኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ የራቀ ስለኾነ ታቦቱን በማክበር እና በደስታ እና በምሥጋና በማጀብ በዓሉን በሰላም ማክበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሰዎች በዓሉን ሲያከብሩ ምን ማድረግ አለባቸው?
በዓሉን ስናከብር ነጠላ መልበስ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ሊቀ ጉባኤ መጋቢ ሳሙኤል የምናከብረው በዓል ምን የተከናወነበት ነው ብለን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ከመጥምቁ ዮሐንስ እና ከክርስቶስ የምንማረው አለ፡፡ ከሁለቱም ትህትናን መማርና መከባርን መተግበር አለብን ብለዋል፡፡ ሃይማኖታችንም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያንም ኾነ በቤተ መንግሥት መከባበር መደማመጥ፣ መሰማማት ከኔ ይልቅ ያንተ ይቅደም ማለትን መማር እና መልመድ አለብን፡፡ “ከተራ የትህትና አንዱ መገለጫ በዓል ነው” ያሉት መምህሩ ከኔ ይልቅ ያንተ ይሁን ማለትን መልመድ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ክርስቶስም ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ያመጣው አንዱ ፍቅር ነው፡፡ ሰዎች ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነን፡፡ ብንጠመቅ ሃይማኖት አለን ብንል እርስ በርሳችን መከባበርና መፈቃቀር ካልቻልን ሃይማኖታችን እና ድካማችን ከንቱ ነው፡፡ ስለዚህ በፍቅር ልንደማመጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በመንግሥት አካላት በኩልም ሌሎችን ዝቅ ብለው የማዳመጥ እና የመስማት ከታች ያለው አካል ደግሞ ከላይ ያለውን አካል የመስማት እና የመደማመጥ ነገር መኖር አለበት ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና ኬኒያ በቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።
Next article“ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያለን አጋርነት ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ጥረቶች ወሳኝ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)