“የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት”

23

ባሕር ዳር: ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን “ከተራ” የሚለውን ቃል ከተረ ወይም ከበበ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው ይሉናል፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም “ከተራ” የሚለውን ቃል ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ ወይም ከለከለ ሲሉ ይፈቱታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር 10 ን ከተራ በሚል በዓል ታከብረዋለች፡፡

የከተራ በዓል የሚከበርበት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓል የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር ነው ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡፡ በታቦታቱ ማደሪያም የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ይጣላል፡፡

የምንጭ ውኃ ደካማ በመኾኑ እንዲጠራቀም ይከተራል፤ ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል ይላሉ በሰሜን ሽዋ ሀገረ ስብከት የሸንኮራ ወረዳ ቤተ ክህነት ኀላፊ ሊቀ ህሩያን ሞገስ ተፈራ፡፡

በከተራ በዓል የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ የራሱ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ምሳሌ አለው የሚሉት ሊቀ ህሩያን ሞገስ ተፈራ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢያሱ 3፡3 ጠቅሰው “የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት” ስለሚል ሕዝቡ ታቦታቱን አጅበው ወደ ማደሪያቸው ያደርሷቸዋል ነው ያሉት፡፡

በበዓለ ጥምቀቱ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ የክርስቶስ ኢየሱስን በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በዋዜማው የመሄዱ ምሳሌ ነው ብለውናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው የሚሉት ኀላፊው ታቦታቱ የጌታችን፣ ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ፣ መዘምራን እና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ምሳሌዎች ናቸው ብለውናል፡፡

ሊቀ ህሩያን በባሕረ ጥምቀቱ ላይ በሚንሳፈፍ ነገር መብራት መደረጉ ደግሞ በእርግብ አምሳል ለወረደው መንፈስ ቅዱስ እና መልዕክት ምሳሌ ነው ብለውናል፡፡ በበዓለ ከተራ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚያመሰግኑበት እና እነርሱም የሚባረኩበት በዓል በመኾኑ አቅማቸው የፈቀደ ጋድ በተባለ ጾም ታቦታቱን ወደ ማደሪያቸው ይሸኛሉ ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
Next article“ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ እንዲመለስ በሰላማዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መስራቷን ትቀጥላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)