የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

19

ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የጥምቀት በዓል ነው። የጥምቀት በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በጋራ እየሠሩ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናግረዋል።

ዲያቆን ኃይሌ ገብሩ የመንገድ ጠረጋ እና የታቦታቱን ማደሪያ በማጽዳት በኩል ወጣቱ ያሳየውን ትብብር በጥምቀት በዓሉም ሊያስቀጥለው ይገባል ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ወጣት ሙሐባው ቀናነው የጥምቀት በዓል ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ወጣቱ ከጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር በሰላም ለማክበር ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌታወይ አብርሃ እንዳሉት በዞኑ 615 አድባራት በከተራ በዓል ጀምረው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይወጣሉ፡፡

በነገው እለትም 528ቱ ወደየ ማደሪያቸው ሲገቡ ቀሪ 87 አድባራት ደግሞ ጥር 12 ወደ ማደሪያቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

ይህ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆየው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ መዋቅሩ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጽዋ ማኅበራት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተመሰሪዎችና እና ከወጣቶች ጋር የጋራ ውይይት ስለማድረጋቸው አስረድተዋል፡፡

በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እስከሚፈጸም ሕዝቡ የተለመደ ትብብሩን ማሳየት እንዳለበትም አቶ ጌታወይ አሳስበዋል፡፡

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
Next article“የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት”