
እንኳን ለከተራና ጥምቀት በዓል አደረሣችሁ!” የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በመላው የሀገራችን አከባቢዎች የሚከበር እንደመሆኑ መጠን እንደዚሁም በሌሎች ክፍለ ዓለማት ጭምር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱና ዓበይት በዓል ነው።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትዉፊቱን ጠብቆ ለዘመናት ሲከበር የመጣ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ለኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ኢኮኖሚ ትስስር መጠናክር፣ ለሀገር ገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ያለው ጠቀሜታም እጅግ ከፍተኛ ነው።
ስለዚህ በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ በሠላምና በድምቀት እንዲከበር ማድረግ ለእምነቱ ተከታዮቹ ብቻ የሚተው ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት በመሆኑ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በዓሉ በሠላም እንዲከበር፣ የሕዝባችን የመከባበርና ትሥሥር ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ የተጠናከረ እንዲሆን እንዲሁም በሀገራዊ ፍቅርና አብሮነት ሀገራዊ አንድነታችን ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እንዲጠናቀር በማድረግ ረገድ የበኩላችንን በጎ አስተዋፅዖ በማበርከት ማክበር ይገባል ሲል ምክር ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል ።
እንደዚሁም በዓሉ የአብሮነት፣ የሠላም፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት መገለጫ ሆኖ እንዲያልፍ መልካም ምኞቱን ምክር ቤቱ ይገልጻል!
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሣችሁ!
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
መልካም በዓል!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!