
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ “እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
በጥምቀት ዕለት ከተፈጸሙ ተአምራት አንዱ አብ በደመና “እርሱን ስሙት” ብሎ መናገሩ ነው። ለምን ነበር “እርሱን ስሙት” ያለው? በዘመኑና በአካባቢው ብዙ የሐሰት ወሬዎች ይወሩ ስለነበር ነው። ራሱ ክርስቶስ የሚናገረውን ትተው ስለ ክርስቶስ የሄደ የመጣ የሚያወራውን የሚሰሙ ብዙ ነበሩ። “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባለው ወሬ የፈታቸው ብዙ ነበሩ።
ትክክለኛውን መረጃ ከትክክለኛው ምንጭ አልሰሙም። እናውቃለን፣ መረጃ አለን ከሚሉ አታላዮች ግን የሆነውንም ያልሆነውንም ይቃርማሉ። በዚህ የተነሣ “እርሱን ስሙት” አላቸው።
የጥምቀት በዓል አንድን መረጃ ከትክክለኛው ምንጭ ብቻ መስማት እንዳለብን የምንማርበት በዓል ነው። ብዙ ፎርጅድ ገንዘቦች ትክክለኛ መስለው ሰዎችን እንደሚያሳስቱት ሁሉ፤ ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎችም እውነተኛ መስለው ሰዎችን ያሳስታሉ። እንዲህ ባለ ጊዜ የተሻለው መንገድ ከትክክለኛው እና ከእውነተኛው ምንጭ መስማት ነው። ምንጭን መምረጥ የጥምቀት አንዱ መልእክት ነው። በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ።
መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል ይሁን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!