“ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ግዴታዋንም ለመወጣት ቁርጠኛ ናት” አቶ ደመቀ መኮንን

39

ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ግዴታዋንም ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ልዕለ ኃያል ያልሆኑ ሆኖም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ያላቸው ሃገራት መካከለኛ ኃይሎች የሚል መጠሪያ አላቸው። የመካከለኛ ኃይል ኃገራት በኃያላኖች መገፋፋት እና መሳሳብ የሚፈጠር ዓለም አቀፍ ውጥረት እና ስጋትን በማርገብ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

ዓለም ባለብዙ ዋልታ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ መካከለኛ ኃይሎች በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጉባኤ ጎን ለጎን ተካሂዷል። በፓናሉ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተወያይ ሆነው በመቅረብ ስለኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት፣ ስለ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እና የአፍሪካ ሚና ሃሳቦችን አካፍለዋል።

በውይይቱ በዓለም ሰላም፣ ደኅንነት እና ምጣኔ ሃብት ቁልፍ ሚና ካላቸው መካከል አንዷ አፍሪካ እንደሆነችም ተናግረዋል። ድህነት፣ የቴክኖሎጂ እጥረት፣ ፋይናንስ፣ የአየር መዛባት የወለዳቸው ድርቅ እና የአካባቢ መራቆት ዋንኛ የአፍሪካ ተግዳሮቶች ቢኾኑም፥ አህጉሪቱ እድሎቿን በመጠቀም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ የእድገት ሃዲድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ብሪክስ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ቁልፍ የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ፣ የኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ አዳዲስ ዕድሎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።

እነኚህን የእድገት አቅሞችና አዲስ የልማት አጋርነትን የሚያስገኝ መሆኑ ኢትዮጵያ ኅብረቱን ለመቀላቀሏ ምክንያት መኾኑን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ ይህም የልማት ሥራዎችን በተሻለ አቅም ለመፈጸም እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ማግኘት ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅባትን ግዴታ ለመወጣትም ቀርጠኛ ናት ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል። ዓለም በአንድ ሀገር የኀይል የበላይነት የምትመራበት ጊዜ እያከተመ፥ ከአንድ በላይ በኾኑ ኀይሎች ወደ መመራት መሸጋገሯ አፍሪካ በባለብዙ ወገን ተቋማት ውስጥ ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራት ያስችላልም ብለዋል።

በዳቮስ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ አቶ ደመቀን ጨምሮ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ከፒተርሰን ኢንስቲትዩት እና ከኢንዶኔዢያ የውጭ ፖሊሲ ማኅበረሰብ የመጡ ምሁራን መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቁ ነገር ሰላም ነው” የጎንደር ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር
Next articleአቶ ተመስገን ጥሩነህ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።