
ባሕር ዳር: ጥር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት አንደኛው ነው፡፡ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች ይከበራል፡፡ የጥምቀት በዓል ከሚደምቅባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ ጎንደር ግንባር ቀደሟ ናት፡፡
ጥምቀት ለጎንደር የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ለቱሪዝም ደግሞ ሰላም ቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡ የጎንደር ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር ሊቀመንበር መምህር ተሻገር ሠርፀድንግል ቱሪዝም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ተጽዕኖ የሚያሳድሩበት ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ በቱሪዝሙ እንቅስቃሴ ጫና ተፈጥሮ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ የሰላም ችግር ሲኖር ጎብኝዎች ወደ መዳረሻዎች እንደማይመጡም አመላክተዋል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መግባት አቁመው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ማቆም በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡
ጎንደር የቱሪዝም ሃብት ባለቤት፣ የቱሪስት መዳረሻ እና በቱሪዝም ተጠቃሚ ናት ያሉት ሊቀመንበሩ በርካታ ሰዎች የሕይወት መሠረታቸውን ቱሪዝም ላይ አድርገው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሲቀዛቀዝ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎዱ ነው የተናገሩት፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሲኖር አስጎብኝዎች፣ የሆቴል ባለሃብቶች፣ አስተናጋጆች፣ ልዩ ልዩ ጥሬ እቃ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚዎች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መቆም አጠቃላይ ኅብረተሰቡን ጎድቷልም ብለዋል፡፡
ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቁ ነገር ሰላም ነው ያሉት ሊቀመንበሩ ሰላምን ለማምጣት ከሁሉም የሚጠበቅ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ከሌለ እንግዶች አይመጡም፣ እንግዶች ካልመጡ ደግሞ ሕይወታቸውን በቱሪዝም ላይ መሠረት ያደረጉ ሰዎች ተጠቃሚ አይኾኑም ነው ያሉት፡፡
ሰላም ከሁሉም ለሁሉም ነው፣ ሰላም የሚመጣበትን ነገር መፈለግ ትልቅ ጥቅም አለውም ብለዋል፡፡ ጥምቀትን በጎንደር ለሚያከብሩ እንግዶች ታሪክን ለመንገር እና በሰላም ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በጥምቀት ከሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ በዓሉ ባለፈ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ጥምቀት በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል፡፡
ጥምቀት የጎንደርን ቱሪዝም የሚያነቃቃ ትልቅ በረከት ነውም ብለዋል፡፡ የጥምቀት በጎንደር በሰላም መከበር ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!