የምክር ቤቱን የአሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።

38

ባሕር ዳር: ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ማሻሻያ ሪፖርት ለምክር ቤቱ ከፍተኛ መሪዎች ቀርቧል፡፡

የማሻሻያ ደንቡ የተጀመረውን ሃገራዊ ሪፎርም፣ የምክር ቤቱን አሁናዊ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን ለመከተል በሚያስችል መልኩ ትኩረት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ማሻሻያ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ለምክር ቤቱ አስተባባሪ እና አማካሪ ኮሚቴዎች ቀርቦ አስተያየት እንደተሰጠበት ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ደንቡን ለማሻሻል በተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመመልከት ከምክር ቤቱ አሁናዊ ሁኔታ ጋር ሊያሠራ የሚችል መኾኑን ለመመልከት ሰፊ ጥናት መደረጉን ጠቁመዋል።

የደንቡ መሻሻል የምክር ቤቱን አሠራር ወጥ እንዲኾን ማስቻልና የታዩ ውስን ክፍተቶችን ለማሻሻል የሚያስችል ነው ያሉት አፈ-ጉባዔው የደንቡ መነሻና መዳረሻ ሕገ መንግሥቱ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የምክር ቤቱ አስተባባሪና አማካሪ ኮሚቴዎች ሀሳብ ሰጥተዋል። ደንቡ የምክር ቤቱን ገለልተኝነት አስጠብቆ በሕግ የተሰጡትን ኀላፊነቶች እንዲወጣ የሚያሰችል መኾን ይገባዋል ነው ያሉት። የደንብ ማሻሻያው በምክር ቤቱ ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”በጦርነት የምናመጣው ሰላም የለም” ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ
Next article“ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቁ ነገር ሰላም ነው” የጎንደር ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር