
ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በተለያዩ ጥፋቶች ተጠርጥረው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በማቆያ እንዲቆዩ እና ሥልጠና እንዲወስዱ የተደረጉ 240 ተጠርጣሪዎች ተለቀዋል።
በምዕራብ አማራ ኮማንድፖስት የባሕር ዳር ተሃድሶ ማዕከል አስተባባሪ አደራ ጋሼ፤ ተጠርጣሪዎቹ ከምርመራ ሂደት በኋላ ሠልጥነው ወጥተውም ለኅብረተሰቡም ለሰላሙም አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተወያይተን ተግባብተናል ብለዋል።
ሰላም በመደፍረሱ ሕዝቡ ለበርካታ ችግሮች ተጋልጧል፤ ስለዚህ ችግሮችን በጋራ ውይይት መፍታት እንጂ እርስ በእርስ በመጎዳዳት ትርፍ የለውም ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄም ምላሽ የሚያገኘው በመመካከር እና በአንድነት ነው ብለዋል።
የሰሜን ምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ የሬጅመንት አምስት አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ገላው “በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ሥልጠና ሲሰጣቸው የቆዩት ወንድሞቻችንን ስንጠብቅ የነበረን ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ ነበር” ብለዋል። የሰላም ዋጋው ከባድ ነው ስለኾነም ሁሉም ለሰላም መቆም አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ እና የባሕር ዳር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ፤ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማረጋጋት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም የሚጠረጠር ካለ ለሰላም ሲባል ማረሚያ ቆይቶ ተመክሮ እና ሥልጠና ወስዶ መለቀቁ የተለመደ አሠራር መኾኑን ተናግረዋል። ስለኾነም ይህንን ታሳቢ ተደርጎ በማረሚያ ቆይታችኋል ብለዋል።
”ሰላም በአንድ ግለሰብም ኾነ በአንድ ወገን ብቻ የሚመጣ አይደለም” ያሉት ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም ”በጦርነትም የምናመጣው ሰላም የለም” ብለዋል። ሁሉም በጋራ ለሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል። “እናንተም ወደ አካባቢያችሁ ስትሄዱ ለሰላም ዘብ እንድትቆሙ ይጠበቅባችኋል” ነው ያሉት።
”አማራ ክልል ከሰላም እጦቱ ጋር ሌሎች ችግሮች ተደራርበውበት እየተሰቃየ ነው” ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ ይህንን ማረጋጋት የሚቻለው በጋራ ስለኾነ ሠልጣኞች ወደየአካባቢያቸው ተመልሰው ለሰላም ከሚሠሩ አካላት ጋር መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
”ሁሉንም ነገር መፍታት የሚቻለው በሰላም ነው፤ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም” ነው ያሉት ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም። በጦርነት ስቃይ እንጂ ደስታ እንደሌለ ጠቅሰው ጥያቄዎችን በሰላም መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!