
ጎንደር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2016 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በጎንደር ከተማ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ሙሉ ዝግጅት ተጠናቅቆ እንግዶችም እየገቡ መኾኑን ከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ የበዓሉን ዝግጅት እና አከባበር በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። ጥምቀት ሃይማኖታዊ በዓል ይሁን እንጅ የጎንደር አከባበሩ በርካታ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ይዘት ያለው ነው ብለዋል።
በተለይም ታሪካዊ እና ባለልዩ ውበት በኾነው ቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የሚከበር መኾኑ በዓሉ በጎንደር ልዩ መልክ እንዲኖረው አስችሎታል ነው ያሉት። በተለይም በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ የጎንደር አብያተ መንግሥታት የእንግዶችን ዐይን የሚስቡ እና ቆይታቸውን የሚያራዝሙ ስለመኾናቸው አስረድተዋል።
ጥምቀት በጎንደር ልዩ ድምቀት አለው፤ ይህንን ድምቀት እና ውበት በቦታው መጥቶ በዐይን በማየት የሚታወቅ እንጅ በንግግር ብቻ ሊገለጥ የማይችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የፊታችን ጥር 11/2016 ዓ.ም የሚከበረው የጥምቀት በዓል እንደሁልጊዜው በአማረ እና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች እና ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ስለ እንግዶች አቀባበል እና አያያዝ ምክክር መደረጉንም ገልጸዋል።
ከንቲባው “የጎንደር ወጣቶች የጥምቀት የድምቀቱ ምንጮች ናቸው” ብለዋል። ወጣቶች የበዓሉ ባለቤቶች በመኾናቸው የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ እና ቀደምት መለያቸው የኾነውን በዓሉን የማድመቅ እሴት የበለጠ ማጉላት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ለጥምቀት በዓል እንግዶች ወደ ጎንደር ቀደም ብለው እየገቡ ስለመኾኑም ከንቲባው ገልጸዋል። ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ እንግዶች እንደሚመጡም አንስተዋል። በጥምቀት ሰበብ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ጠቁመው በከተማዋ ኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች አስፈላጊው ሁሉ የልማት አማራጭ ተመቻችቷል ብለዋል።
ለአብነትም 32 ሄክታር መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ ኾኖ ለአልሚዎች ተመቻችቷል ነው ያሉት። ለመኖሪያ እና ለንግድ አገልግሎት የሚውል ከ14 ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ ለሊዝ ሽያጨ እንደተዘጋጀ አስረድተዋል።
ከንቲባው እንግዶች ወደ ጎንደር በመምጣት የከተማዋን እና የአካባቢውን ባሕል፣ ቅርስ እንዲሁም የሕዝቡን እሴት እንዲያውቁ፤ በአካባቢው ላይ አልምተውም ለራሳቸው ተጠቅመው ለሀገርም ኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!