
ደሴ: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጥምቀት በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ በደሴ ከተማም በዓሉ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በሃይማኖታዊ ዝማሬ እና በልዩ ልዩ ኹነቶች ይከበራል።
በከተማዋ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የደሴ ከተማ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታውቋል፡፡ የመምሪያው ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ሰይድ አሊ ከእምነቱ አባቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም እንዲከበር የሚያስችል ውይይት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ የሌሎች እምነት አባቶችም በዓሉ በሰላም በሚከበርበት ሁኔታ ላይ በተካሄደው ውይይት መሳተፋቸውን የገለጹት ምክትል ኮማንደር ሰይድ የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ የተለመደውን ፍቅር እና አብሮነት ለማሳየት መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
ከጸጥታ ኀይሉ ባለፈ የሰላሙ ባለቤት ሕዝብ በመኾኑ የእምነቱ ተከታዮች እና ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበዓሉ አከባበር ላይ የጸጥታ ስጋት ሊኾን የሚችል የተለየ ነገር ሲያስተውሉ ለጸጥታ ኀይሉ ጥቆማ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!